የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለማድረግ ወደ ሲንጋፖር ያቀናው አርሰናል በወዳጅነት ጨዋታ ኤ ሲ ሚላንን አሸንፏል፡፡ በሲንጋፖር ናሽናል ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አርሰናል 1ለ0 ማሸነፍ ችሏል ፡፡
የማሸነፊያ ግቡን ቡካዮ ሳካ 52ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል ፡፡ በጨዋታው አርሰናል ከፍተኛ ብልጫ ወስዷል ፡፡ የቀድሞ አሰልጣኛቸው ማሲሚሊያኖ አሌግሪን መልሰው የቀጠሩት ኤ ሲ ሚላኖች በአንፃሩ ይበልጥ መከላከሉ ላይ አመዝነው ተጫውተዋል ፡፡
መድፈኞቹ ካስፈረሟቸው ተጫዋቾች ውስጥ ክርስቲያን ኖርጋርድ ፣ ማርቲን ዙብሜንዲ እና ግብ ጠባቂው ኬፓ አሪዛባላጋ በጨዋታው ተሳትፈዋል ፡፡
ከቼልሲ ጋር የዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይ የተሳተፈው ኖኒ ማዱኤኬ እረፍት ስለተሰጠው ከስብስቡ ጋር አይገኝም ፡፡
ሚካኤል አርቴታ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የ15 ዓመቱ ማክስ ዶውማን ተቀይሮ ገብቶ እንዲጨዋት አድርጓል ፡፡
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በቀጣይ አራት የወዳጅነት ጨዋታ ያከናውናል ፡፡ በሲንጋፖር ከኒውካስትል ፣ በሆንግ ኮንግ ከቶተንሃም ፣ በሜዳው ኤምሬትስ ደግሞ ከቪያሪያል እና አትሌቲክ ቢልባኦ ጋር ይጫወታል ፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ