ወንዝና አካባቢን የበከሉ ሁለት ተቋማት 600ሺህ ብር መቀጣታቸዉን የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታዉቋል።
የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ሁለት ተቋማት ወንዝና አካባቢን በመበከላቸዉ እያንዳንዳቸዉ 300ሺህ ብር መቀጣታቸዉን ለኤኤምኤን ዲጂታል ሚዲያ ተናግረዋል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ቦታው ይርጋሀይሌ አካባቢ የሚገኘው ስኬት ህንፃ ኃላፊነቱ የተረጋገጠ የግል ማህበር የዝናብ ውሀ ሽፋን በማድረግ የሽንት ቤት ፍሳሽ በመልቀቅ አካባቢውን በመበከል ደንብ በመተላለፉ 300 ሺ ብር መቀጣቱን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ኖህ ሪል ሰቴት ወደ ወንዝ ቆሻሻ በመጣሉ 300ሺ ብር መቀጣቱን ጨምረዉ ገልጸዋል።
ተቋማቶቹ ከዚህ በፊት ግንዛቤ የተፈጠረላቸው ቢሆንም ደንቡን ማክበር አልቻሉም።
የክረምቱን የዝናብ ውሀ ሽፋን በማድረግ ቆሻሻ የሚለቁ ግለሰቦችና ተቋማት ከድርጊታቸዉ ሊቆጠቡ እንደሚገባ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ አሳስበዋል።
የፍሳሽ ማስወገጃዎችን መድፈን ለጎርፍ አደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ ነዋሪዎች ከመሠል ድርጊቶች ሊቆጠቡ ይገባል።
የመዲናዋ ነዋሪዎችም ደንብ ተላልፈዉ የተገኙ ግለሰቦችንና ተቋማትን ተከታትሎ ለባለስልጣኑ መረጃ በመስጠት ሀገራዊ ግዴታቸዉን ሊወጡ ይገባል።
በወንድማገኝ አሰፋ