በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መንግስት አዘጋጅነት በአፍሪካ ኢኮኖሚ መሰብሰቢያ አዳራሽ ላለፉት ቀናት በተለያዩ መረሃግብሮች ሲካሄድ የቆየው 2ተኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ጉባኤ ዛሬ ማምሻውን ተጠናቋል።
የኢ.ፊ.ዲ.ሪ.ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ሽግግር እና ልዑላዊነት እንዲሁም የምግብ ዋስትና በስንዴ ምርት እራስን ለመቻል የተደረጉ ጥረቶች ፤ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ወደ ገበያ በማቅረብ ትርፍ አምራች በመሆን የተሻለ ማረጋገጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተመድ 2030 ዘላዊ የልማት ግብ እንዲሳካ አገራት ያደረጉት ጥረት እና ማህበራዊ ለውጥ እንዲመጣ ያሳኩት በእጅጉ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል ።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ የምግብ ስርዓት አጀንዳ ክብር፣ ነፃነት እና ለሰው ልጆች ፍትህን መመኝት ውጤት ነው ብለዋል።

በዓለም ላይ በመስኖ ልማት ፣በግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ፣ምርታማነትን በማሳደግ የተሰሩ ስራዎች የተሳካ ፖሊስ ውጤት ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል ።
በጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ልማት ትብብር ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ስቴፋኖ ጋቲ በምግብ ስርዓት ዘርፈ ብዙ በሆነው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ በአገራት የታዬ ድንቅ ለውጦች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል ።
የተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና ሞሀመድ በዓለም ላይ የተመድ የዘላቂ ልማት ግብ አንዲሳካ የተደረጉ ትብብሮችን አድንቀዋል ። ይህ ጉባኤ የኢትዮጵያ መንግስት ያደረገው ዝግጅት እና የጣሊያን መንግስት ያደረጉት ድጋፍ ሊመሰግን ይገባል ማለታቸዉን ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
ምክትል ዋና ፀሐፊዋ አሚና ሞሀመድ በኢትዮጵያ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚ ዘርፍ በምግብ ስርዓት ለውጥ የታየው ቁርጠኝነት ሊመሰገን ይገባል ብለዋል ።

ጠንካራ ቅንጅት ፤ስትራቴጂካዊ ውሳኔዎች እና የግብርና የፋይናንስ ስርዓት መሻሻል በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ስርዓት እንዲሻሻል መሆኑን ተናግረዋል።ለአርሶአደሮች የተረጋጋ አካባቢ እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ጫና ተቋቁመው ምርታማ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊሰሩ እንደሚገባ አፅንኦት ተሰጥተዋል ።
በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው ከ5ሺ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበት ፣ከ30 በላይ የጎንዮሽ ውይይቶች የተካሄዱበት 180 በላይ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ሽፋን የሰጡት በአዲስአበባ የተካሄደ 2ተኛው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ማምሻውን በስኬት ተጠናቋል።