የአንድ ጀንበሩን እጆች የሚፈልገውምዕራፍ

You are currently viewing የአንድ ጀንበሩን እጆች የሚፈልገውምዕራፍ

•   በተከላው መርሃ ግብር እንደተሳተፍነው ሁሉ በእንክካቤውም ተግተን እንቀጥላለን ሲሉ በዘንድሮው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በግንፍሌ ወንዝ አካባቢ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ

ላለፉት 6 ዓመታት ኢትዮጵያውያን ተባብረው ችግኝ ሲተክሉ ከርመዋል። ዘንድሮም የክረምቱ ወቅት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለ7ኛ ዙር በመርሃ ግብሩ እየተሳተፉ ይገኛሉ። በመደበኛነት ከሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባሻገር በየዓመቱ በሚከናወነው የአንድ ጀንበር መርሃ ግብርም በነቂስ ወጥተው ይሳተፋሉ። ዘንድሮም በመላው ኢትዮጵያ 29 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች በመርሃ ግብሩ ተሳትፈዋል።

የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃም በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ ተከናውኗል። በግንፍሌ ወንዝ ዳርቻ ተገኝተን የችግኝ ተከላውን ሂደት ቃኝተናል። ለመሆኑ ለተከላው በነቂስ እንደተወጣው ሁሉ በእንክብካቤውም ላለመጉደል ምን ማድረግ ይገባል? ስንል በስፍራው ለተገኙ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች ላቀረብነው ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።

በግንፍሌ ወንዝ አካባቢ በተካሄደው የዘንድሮው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በነቂስ ወጥተው የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች በተከላ መርሃ ግብሩ በትብብር እንደተሳተፍነው ሁሉ በእንክካቤውም ተግተን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የቀበናና አካባቢው ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል መከላከል ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ፈይሳ ዘውዴ በቀበና ወንዝ አካባቢ በተዘጋጀው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ከሌሎች የፖሊስ አባላትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ችግኝ ሲተክሉ አግኝተን አነጋግረናቸዋል፡፡ በቆይታችን፣ “ፖሊስ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ከማስጠበቅ ጎን ለጎን እንደዚህ አይነት ለትውልድ ትልቅ አሻራ በሚጣልባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነው” ብለውናል፡፡

ምክትል ኢንስፔክተር ፈይሳ እና ሌሎች ባልደረቦቻቸው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በተከናወኑ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ተሳታፊ እንደነበሩ አስታውሰው፣ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን በመጠበቅና በመንከባከብ ረገድም የጎላ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

እንደምክትል ኢንስፔክተሩ ገለፃ፣ ችግኞችን መንከባከብና መጠበቅ በጊዜ የሚወሰን አይደለም፡፡ ችግኝ መትከል ልክ ልጅ ወልዶ እንደማሳደግ ነው፡፡ አንድ ልጅ ተወልዶ ለማደግ የወላጆቹን እንክብካቤና ድጋፍ እንደሚፈልግ ሁሉ ችግኞችም ከተተከሉበት ጊዜ ጀምሮ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

ችግኞች የተተከሉበት አካባቢን በመከለል የቤት እንስሳት ጉዳት እንዳያደርሱ መጠበቅ ብሎም በበጋ ወራት እንዳይደርቁ ውሃ ማጠጣት እንደሚገባ አስታውሰው፣ የፖሊስ አባላቱም የተከሏቸውን ችግኞች ልክ እንደመደበኛ ስራቸው በመመልከት አስፈላጊውን ክትትልና እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ አሰገደች አካሉ በግንፍሌ ወንዝ ዳር በተካሄደው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሲሆኑ፣ በወቅቱ በሰጡን አስተያየት ችግኝ መትከል የተተኪውን ትውልድ ህይወት ማስቀጠል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ዛሬ በተከሉት ችግኝ ነገ ልጆቻቸው ከፀሐይ የሚጠለሉበት፣ ንፁህ አየር የሚተነፍሱበት ከመሆን አልፎ ፅዱ፣ አረንጓዴና ያማረ አካባቢን ለትውልድ የማስረከብ ኃላፊነትን የሚወጡበት ጥሩ መሰረት እያኖሩ እንደሆነ ገልፀው፣ ችግኝን ተንከባክቦ ማሳደግ ለሰፈራቸው ብሎም ለከተማዋ ውበትና ልማት ትልቅ አስተዋፅኦ እዳለው ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ አያንቱ ገለታ በዘንድሮው የአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በግንፍሌ ወንዝ ዳርቻ ችግኝ ሲተክሉ አግኝተን ባነጋገርናቸው ወቅት፣ አንድ ሆነን ችግኞችን የምንተክለው በመሬት መራቆት ምክንያት ከሚደርስብን የጎርፍ አደጋ ለመዳን ብቻ ሳይሆን ምግብም ለማግኘት ነው ብለዋል፡፡

“ችግኝ የደን ሽፋናችንን ያሳድጋል፤ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርታማነታችንን ለመጨመርም ስለሚያግዝ በተከላው ላይ በትኩረት እየተሳተፍኩ ነው፡፡ እንክብካቤው ላይም እበረታለሁ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተካ ደመቀ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደገለፁት፣ በክፍለ ከተማው በአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አስራ ሰባት አካባቢዎች ተከናውኗል፡፡

በችግኝ ተከላው ከ21 ሺህ 690 የሚበልጡ የክፍለ ከተማው የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 12 ሺህ 185 ሴቶችና 9 ሺህ 512 ወንዶች መሆናቸውን ነው ያስታወቁት፡፡ በእለቱ እንደ ክፍለ ከተማ 16 ሺህ 355 ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ፣ 23 ሺህ 59 ችግኞች ተተክለዋል፡፡

ከተተከሉ ችግኞች 14 ሺህ 604 የጥላ፣ 2 ሺህ 772 የውበት አበባዎችና 5 ሺህ 683 የፍራፍሬ መሆናቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ አመራሮች እና በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ስለ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ ያለው ተሳትፎና ግንዛቤ እለት ከእለት እየተሻሻለና እየጎለበተ መጥቷል ብለው፣ በመርሃ ግብሩ ህብረተሰቡ በጊዜ ወጥቶ መሳተፉን ገልፀዋል፡፡ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከለውን ተንከባክቦ በማፅደቅ ረገድም ጠንካራ አመለካከት እና ግንዛቤ ያለው ማህበረሰብ መፈጠሩን ጠቁመው፣ ለዚህም ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት የተተከሉ ችግኞች የፅድቀት መጠን 89 በመቶ መሆኑን እንደማሳያ አንስተዋል፡

በየወረዳው ያሉ ነዋሪዎች ከሚያከናውኑት የእንክብካቤ ስራ በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ የመደባቸው በ17 ማህበር የተደራጁ 170 የሚጠጉ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወገኖች በቋሚነት የእንክብካቤውን ስራ እንደሚሰሩ ጠቁመው፣ ይህ ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞች ከቀድሞው በበለጠ የመፅደቅ እድል እንዲኖራቸው ያስችላልም ብለዋል፡፡

በዘንድሮው የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በአራዳ ክፍለ ከተማ ተሳትፎ ካደረጉ የከተማና የፌዴራል እንዲሁም የግል ተቋማት መካከልም ከንቲባ ፅህፈት ቤት፣ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር እና አቤት ሆስፒታል ተጠቃሾች ናቸው። የችግኝ ተከላውም በግንፍሌና ቀበና ወንዝ ዳርቻ፣ ጃንሜዳ፣ በክፍለ ከተማው ወረዳ 2 የሙስሊም መቃብር፣ በወረዳ 1 በሚገኘው ጆን.ኤፍ.ኬኔዲ ትምህርት ቤት እንዲሁም ወረዳ 1 የጎርደሜ ወንዝ ዳርቻን ጨምሮ በ17 የተለያዩ አካባቢዎች ነው የተከናወነው፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 አስተዳደር የውበትና አረንጓዴ ልማት ፅህፈት ቤት ባለሙያ  አቶ ባየው ብርሃኔ ችግኞችን የመትከል ፋይዳ ቀላል አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ከዛፍ ምርቶቻቸው ለመጠቀም፤ የተጎዱ መሬቶች መልሰው እንዲለሙ ለማድረግ፤ አካባቢን ለማስዋብ፣ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የተፈጥሮን ሚዛን ለመጠበቅ፣ በካይ ነገሮችን ለመቀነስ፣ የአየር ጥራት ለማሻሻል በጥቅሉ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከፍተኛ አስተዋፆኦ እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡

ባለሙያው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ውጤታማ እንዲሆኑ በሙያቸው ከማገዝ አልፈው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንደሀገር ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በግላቸውም ችግኝ በመትከል የግል ድርሻቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ገልፀው፣ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ የፅድቀት መጠናቸው ከፍ እንዲል ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ባለሙያው ገለፃ፣ የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ በተለይ በበጋ ወራት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ባለሃብቶችን በማስተባበር ውሃ በማጠጣትና በመኮትኮት እንክብካቤ ሲደረግ ቆይቷል፡፡

በግንፍሌ እና ቀበና ወንዝ አካባቢ ከሁለት ዓመት በፊት የተተከሉ ችግኞች የፅድቀት መጠን ለዚህ ማሳያ ናቸው ያሉት ባለሙያው፣ የተተከሉት ችግኞች ሙሉ በሙሉ በመፅደቃቸው ድካም ለተጫጫነው ማረፊያ ለአካባቢውም ልዩ ውበትን አጎናፅፈውታል፡፡

ዘንድሮም ባሉት ክፍት ቦታዎች እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ዘይቱን እና ፓፓያ ያሉ ለምግብነት የሚውሉ የፍራፍሬ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ ችግኝ ተክሎ መተው ብቻ ሳይሆን ተከታታይነት ያለው የእንክብካቤ ስራ በቀጣይ እንደሚሰራም ነው ያረጋገጡት፡፡

የተተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ ከጉድጓድ ቁፋሮ ጀምሮ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል ያሉት ባለሙያው፣ በተለይ በንቅናቄ በሚተከልበት ወቅት ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል ከነ ፕላስቲኩ መትከል፣ በደንብ አፈር ሳያለብሱ መተው፣ እንዲሁም ችግኞቹን በተዘጋጀላቸው ጉድጓድ ከመትከል ይልቅ ሜዳ ላይ ጥሎ መሄድ የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ከንቅናቄው በኋላ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የመስክ ባለሙያዎችና የቢሮ ሰራተኞች በተተከሉ አካባቢዎች እየተዟዟሩ በአግባቡ ያልተተከሉትን በመትከል፣ የወደቁትን በመሰብሰብና አፈር ያልለበሱትን በማልበስ የማስተካከል ስራ ይሰራሉ፡፡

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review