ሰላም፣ አንድነትና አብሮነትን በማጎልበት አገሪቷን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ በማሻገር ረገድ የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ ነው

You are currently viewing ሰላም፣ አንድነትና አብሮነትን በማጎልበት አገሪቷን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ በማሻገር ረገድ የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ ነው

‎AMN- ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም

‎ሰላም፣ አንድነትና አብሮነትን በማጎልበት አገሪቷን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ በማሻገር ረገድ የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ መሆን እንደሚገባው የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሓፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተናገሩ።

‎”ኃይማኖቶች ለሰላም፣ለአንድነት እና ለአብሮነት”በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሰላም ኮንፍረንስ በሐረር ከተማ እየተካሄደ ነው።

‎በጉባዔው መክፈቻ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሓፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደተናገሩት፣ የኢትዮዽያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ግጭትን በማስቆምና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር በማድረግ በኩል አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

‎የሃይማኖት ተቋማት በዘላቂ ሰላም ግንባታ ሂደት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፣ ተቋማቱ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመሙላት በዘርፉ እያበረከቱ ያለውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

‎የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰላምን ለማስፈንና አፅንቶ ለማዝለቅ የጀመረውን የሰላም ጉባኤ በቀጣይም አጠናክሮ በመቀጠል ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች አገርን ማስረከብ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

‎”ቀደምት አባቶቻችን በሰላም፣ በአብሮነትና በአንድነት ላይ ታሪካዊ አሻራ አስቀምጠው አልፈዋል”ያሉት ጠቅላይ ጸሃፊው፣ ይህንን የማጎልበት ሃላፊነታችንን መወጣት ይገባል ብለዋል።

‎የሰላም ጉባኤው አላማም በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ አለመግባባቶች እንዲቆሙና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረግ ሁለንተናዊ ጥረት አካል እንደሆነ ጠቁመዋል።

‎ሰላም፣ አንድነትና አብሮነትን በማጎልበት አገሪቷን ወደ ተሻለ የእድገት ደረጃ በማሻገር ረገድ የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ በመሆኑ ያንን ሚናችንን መወጣት አለብን ብለዋል።

‎በጉባዔው የታደሙት የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር በበኩላቸው፣ የሃይማኖት ተቋማት በቤተ እምነቶች ለምዕመናኑ የሚሰጡት የሰላም አስተምህሮ መጎልበት እንዳለበት አመልክተዋል።

‎የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰላምን ለማስፈንና አፅንቶ ለማዝለቅ የጀመረውን ተግባር በቀጣይም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስረድተዋል።

‎የሐረሪ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ሰብሳቢ ሼህ አብዱሰላም ጅብሪል፤ ጉባዔው የሃይማኖት ተቋማት በየቤተ እምነታችን ለምዕመኑ የምንሰጠው የሰላም አስተምህሮ፣ እርቅ እና ይቅርታን የሚያጎለብት እንዲሁም ለሀገር ሰላም መስፈን አስተዋጽኦ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።

‎በጉባኤው ላይ የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አባላትና የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶች ተወካዮች እንዲሁም ከተለያዩ ክልሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ሌሎች ከፍተኛ የክልሉ የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል ሲል ተዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review