ከ8 በላይ ሶፍትዌሮችን በማበልፀግ ወንጀልን ለመከላከል እየተጠቀመበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ

You are currently viewing ከ8 በላይ ሶፍትዌሮችን በማበልፀግ ወንጀልን ለመከላከል እየተጠቀመበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ

AMN- ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ ከ8 በላይ ሶፍትዌሮችን በማበልፀግ ወንጀልን ለመከላከል እና የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ እየተጠቀመበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ተናገሩ።

በፌዴራል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ያከናወናቸውን የለውጥ ስራዎች ጎብኝተዋል፡፡

የአዲስአበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል እና ምርመራ ስራዎቹን በቴክኖሎጂ ከማገዝ ባለፈ እራሱን ከህብረተሰቡ ጋር ለማስተሳሰር የሄደበት ርቀት የሚደነቅ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለፀዋል።

በአፍሪካ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በተደራጀ መንገድ በብቃት የሚመራ ተቋም በመገንባት ረገድ ከለውጡ ዓመታት በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሁሉም መስኮች የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል።

እንደሀገር የፖሊስ ስራን ለማዘመንና ተገቢውን ክብርና ከፍታ እንዲያገኝ በሁሉም ዘርፍ እራስን የማዘመን ስራ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፣ የሪፎርም ስራ መስራታቸው እና ከተቋማት ጋር በቅንጅት መንቀሳቀሳቸው ውጤት ማስገኘቱን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፣ የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የወንጀል ምርመራና የቁጥጥር ስርዓት በመዘርጋት ህብረተሰቡን የሰላሙ ተጠቃሚ ለማድረግ ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ያከናወናቸው ተግባራት የጎበኙት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ ኮምሽኑ በቴክኖሎጂ እራሱን ከህብረተሰቡ ጋር ለማስተሳሰር የሄደበት ርቀት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

ፖሊስ የህብረተሰቡን ሰላም በመጠበቅ፣ የከተማዋን ጸጥታ እና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያደርገው ጥረት ከሰው ሀይል ጀምሮ በግብዓት እና በቴክኖሎጂ እራሱን ማሳደግ አለበት ያሉት ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የአዲስ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የጀመራቸውን ውጤታማ ስራዋች ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ማስቀጠል እንዳለበት ምክራቸውን ለግሰዋል።

በአሸናፊ በላይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review