የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ወደ ሞስኮ ከማቅናታቸው በፊት፣ ዘለንስኪ ከትራምፕ ጋር በሩስያ ላይ በተጣሉ ማዕቀቦች፣ በመከላከያ ትብብር እና በሰው አልባ ድሮን ምርቶች ላይ መወያየታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ዘለንስኪ ከትራምፕ ጋር ውጤታማ ውይይት በማድረጋቸው ትራምፕን አመስግነዋል።
ትራምፕ ቀደም ሲል ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እስከ አርብ ድረስ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ካልቻለች፣ ከፍተኛ ማዕቀብ እንደሚጣልባት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
ልዩ መልዕክተኛው ዛሬ ወደ ሞስኮ አቅንተው ከፑቲን ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል ተብሏል።
ሰኞ እለት በተሰጠው መግለጫ ትራምፕ የሩሲያ ዘይት ገዢ በሆነችው በህንድ ላይ ከባድ አዲስ ታሪፍ እንደሚጣልባት አስታውቋል ።
ሞስኮ በበኩሏ፣ ሀገራት ከሩሲያ ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት እንዲያቋርጡ ለማስገደድ የተደረገው ሙከራ ህገወጥነት ነው ብላለች።
ትራምፕ፣ ባለፈው ወር በሰጡት መግለጫ፣ አሜሪካ ለሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት አባል ሀገራት ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን የጦር መሳሪያዎች ትሸጣለች፤ ከዚያም ወደ ኪየቭ እንደሚያስተላልፉ መናገራቸውን ተከትሎ በዚህ ሳምንት ዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ኔዘርላንድስ እና ስዊድን በዚህ እቅድ መሠረት ከአሜሪካ የጦር መሳሪያ በመግዛት የመጀመሪያዎቹ ሀገራት እንደሚሆኑ ታውቋል።
ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ግጭቱን በአንድ ቀን ውስጥ ማስቆም እንደሚችሉ ደጋግመው ይናገሩ ነበር።
ፑቲን ከኪየቭ ጋር የሚደረገውን ውይይት በአዎንታዊ መልኩ እንደሚመለከቱት ተናግረው፣ ሁሉም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች የሚከሰቱት በተጋነነ መልኩ ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል ።
በብርሃኑ ወርቅነህ