የማህበራዊ ሚዲያ ተፅእኖ ፈጣሪ፣ ዓለም አቀፍ ቭሎገር፣ ዩቲዩበር እና የባህል አምባሳደር የሆነው ጋናዊው ዎድ ማያ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝቷል፡
ከአምስት አመት በፊት የመጀመሪያ የዩቲዩብ ቪዲዮዎቹን መቅረጽ የጀመረው አዲስ አበባ ከተማ እንደሆነ ለኤ ኤም ኤን የተናገረው ዎድ፣ ከአምስት አመት በኋላ ዳግም ተመልሶ ሃገሪቷ ያለችበትን አቋም በተሻለ መንገድ ለመላው አፍሪካ ለማሳየት እንደመጣም ገልጿል፡፡
የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ተዘዋውሮ በርካታ ስፍራዎችን እንደጎበኘ የሚናገረው ጋናዊው ዎድ ማያ፣ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተገኝቶ የተመለከተው ነገር እንዳስደነቀውም አንስቷል፡፡
በፓን አፍሪካን እንቅስቃሴዎች ላይ እጅጉን ተሳታፊ የሆነው ጋናዊው ዎድ ማያ፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት ቀንዲል መሆኗን ለማወቅ የዓድዋ ታሪክን ብቻ ማንበብ ይበቃል ብሏል፡፡
አብዛኛው የአፍሪካ ሀገር በነጮች የተገዙ ናቸዉ ያለው ዎድ ማያ፣ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን ታሪኳ ልዩ ነው ብሏል፡፡
እስከዛሬ በታሪክ ብቻ ኢትዮጵያ ብቸኛ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ሃገር ሲባል እንደሚሰማና ዛሬ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተገኝቶ ታሪኩን ቁልጭ ባለ መልኩ በመመልከቱ መደሰቱን በአንደናቆት ገልጿል፡፡
ዎድ ማያ አክሎም አያት ቅድመ አያቶቻችን አንድ በመሆን ይህን የመሰለ የጀግንነት ታሪክ በደማቅ ቀለም ካሰፈሩ፣ ያሁኑ ትውልድ ከዚህ ሊማር የሚገባው ብዙ ነገር አለ ብሏል፡፡
ዎድ በመጨረሻም አፍሪካዊ ነኝ የሚል ሁሉ የአህጉሪቱ ኩራት የሆነውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሊጎበኙ ይገባል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡