የጃፓኗ ሂሮሺማ የአቶሚክ ቦንብ ጥቃትን በምታስብበት 80ኛ ዓመት የመታሰቢያ ሰነ ስርዓት ላይ የኒውክሌር መሳሪያዎችን አደገኝነት አስጠንቅቃች፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሂሮሺማ የሰላም መታሰቢያ ፓርክ በመሰብሰብ እ.ኤ.አ በ1945 በአሜሪካ በተሰነዘረው ዩራኒየም ቦምብ የደረሰውን እልቂት አስበዋል።
በጥቃቱ 78 ሺህ ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስም ለጨረር በመጋለጣቸው ምክንያት ተጨማሪ ብዙ ሰዎች ማለፋቸው ይታወሳል።
በመታሰቢያ ስነ-ስርአቱ ላይ አሜሪካ እና እስራኤልን ጨምሮ ከ120 ሃገራት የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
አቶሚክ ቦንቡ ፈነዳበት በተባለው ትክክለኛ ሰዓት ለደቂቃዎች በቆየ ዝምታ ታስቧል።
የሂሮሺማ ከንቲባ ካዙሚ ማትሱይ በመታሰቢያ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ተቀባይነቱ እየጨመረ የመጣውን የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንደ አስፈላጊ የመከላከያ ስትራቴጂ መጠቀምን የዓለም መሪዎች ውድቅ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ይህ አካሄድ ከሂሮሺማ እና ናጋሳኪ የተወሰደውን ትምህርት መዘንጋትና በዓለም አቀፍ የሰላም ግንባታ ላይ የተደረጉ ጥረቶችን የሚንድ መሆኑንም ከንቲባው መጠቆማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በሊያት ካሳሁን