ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በበጀት ዓመቱ ከመነጨው ሃይል ውስጥ 33 ነጥብ 2 በመቶ በማመንጨት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ተገለጸ

You are currently viewing ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በበጀት ዓመቱ ከመነጨው ሃይል ውስጥ 33 ነጥብ 2 በመቶ በማመንጨት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ተገለጸ
  • Post category:ልማት

AMN ነሐሴ 2/2017

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅዱን አስመልክቶ በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ በበጀት ዓመቱ ከመነጨው ሃይል ውስጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 33 ነጥብ 2 በመቶ እንዲሁም ጊቤ 3 ኃይል ማመንጫ 24 ነጥብ 2 በመቶ ኃይል በማመንጨት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበራቸው አስታዉቋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ (ኢ/ር) እንዳሉት፥ በበጀት ዓመቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ባሉት 20 የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች 25 ሺህ 423 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማምረት ታቅዶ 29 ሺ 480 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማምረት ተችሏል።

በተጠናቀቀው የ2017 በጀት አመት ለአገር ውስጥና ለውጭ አገራት ከቀረበው የኃይል ሽያጭ እንዲሁም ተጓዳኝ አገልግሎቶች 75 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ነው የገለፁት።

መንግስት ተግባራዊ ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተቋሙ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲያድግ ማስቻሉን ገልጸው፤ይህም በ2016 በጀት አመት ያገኘው የ140 ሚሊየን ዶላር በ2017 በጀት አመት ወደ 388 ሚሊየን ዶላር እንዲያድግ ማስቻሉን ገልፀዋል።

በበጀት አመቱ አራት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ እንደነበሩ ጠቁመው፤ ከእነዚህም መካከል ሁለቱ በ2018 ዓ.ም ወደ ስራ እንደሚገቡም ተናግረዋል።

የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም 71 ነጥብ በመቶ መድረሱን ጠቁመው፤የአይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም ከ85 በመቶ በላይ መድረሱን ገልፀዋል።

በግንባታ ላይ የነበሩ የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ፕሮጀክቶች ውስጥ አምስቱ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ስርቆትና በአንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ የፀጥታ ችግሮች በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ማስረዳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review