አስር ክልሎች መደበኛ የሰብዓዊ ድጋፍን በራሳቸው ማሟላት መቻላቸዉን ኮሚሽኑ ገለጸ

You are currently viewing አስር ክልሎች መደበኛ የሰብዓዊ ድጋፍን በራሳቸው ማሟላት መቻላቸዉን ኮሚሽኑ ገለጸ

AMN ነሐሴ 3/2017

ተረጂነትን ለማስቀረት በተከናወኑ ተግባራት አስር ክልሎች የትኛውንም ዓይነት መደበኛ የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት በራሳቸው ማሟላት መቻላቸውን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም የአደጋ ስጋት አመራር ጉዳዮች የብሔራዊ ደህንነት፣ የሰብዓዊ መብትና የማህበራዊ ፍትህ አጀንዳዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተጨማሪም የሰላም ግንባታ እና የዘላቂ ልማት ማረጋገጫ ተደርጎ ይወሰዳል ነው ያሉት።

በመሆኑም እነዚህን ሀገራዊ ጉዳዮች በአንድ ላይ ቀምሮ ለመስራት የአደጋ ስጋት አመራር ስራን በተጠናከረ መልኩ ማከናወን በዘርፉ ተጨማሪ አቅምና ስኬትን ለማረጋገጥ ያግዛል።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ያከናወነችው ተግባር የሚበረታታና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመው፤ የተባበሩት መንግስታት የምግብ ስርዓት ጉባኤን በተሳካ ሁኔታ ማካሔዷ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።

የሰብዓዊ ድጋፍን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራትም አስር ክልሎች የትኛውንም ዓይነት መደበኛ የሰብዓዊ ድጋፍ አገልግሎት በራሳቸው በማሟላት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ለሰብዓዊ ድጋፍ ተብሎ ከውጭ ይገባ የነበረውን የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት በራስ አቅም መሸፈን መቻሉንም ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት።

ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሒደት ትልቁ ማንሰራራት በሚል የተመዘገበ ስኬት መሆኑን ገልጸው፤ ከሶስት አመት በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ የነበረውን የተረጂዎች ቁጥር በ86 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል ብለዋል።

ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን በተግባር የሚያረጋግጥ መሆኑን ነው ያብራሩት።

ክልሎች ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል የምርት አቅርቦትን በሚመለከት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 100ሺህ ሔክታር መሬት መታረሱን አብራርተዋል።

ይህንን ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ በመሆኑ በዘንድሮ መኸር ወቅትም የተሻለ የምርት አቅምን ለመፍጠር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ እየተሰራ ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

ለአብነትም የአደጋ ምላሽ ፈንድ ማቋቋም፣ የመዋቅር ማሻሻያና የክምችት አቅምን መጨመር ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review