የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ማምሻዉን የፒያሳን መልሶ ማልማት፣ በ 4 ኪሎ እንጦጦ ፣ጉለሌ የእፅዋት ማዕከል የኮሪደር ልማትና የእንጦጦ ወዳጅነት አደባባይ ፒኮክ ፓርክ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ስራ ላይ የላቀ አስተዋፆ ላበረከቱ አካላት የእዉቅናና የምስጋና ማበረታቻ ማካሄዳቸዉን ገልጸዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት ራዕያችንን ተጋርታችሁ ደማቅ ታሪክ ለፃፋችሁ የኢትዮጵያ ልጆች በሙሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ብለዋል።
በሽታ አምጪ የነበረዉን የወንዞቻችንን ጠረን ተቋቁማችሁ ፣ ለክረምቱ ዝናብ እና ቁር ሳትበገሩ ፣ የጤና ሁኔታችሁን አደጋ ላይ ጥላችሁ ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ ራዕያችንን ተጋርታችሁ ይህንን የመሰለ መጪዉ ትዉልድና መላዉ አገር ወዳድ ኢትዮዽያዊ የሚኮራበትን አስደናቂ ስራ በመስራታችሁ ወደፊትም ታሪክ ሲዘክራችሁ ይኖራል ሲሉ ገልጸዋል።
በተለይም የወንዝ ዳርቻ ልማት ከ2012 ዓ.ም አንስቶ የዉጭ መንግስታትን ፣ ደጋፊ አካላትን እገዛ ጠይቀን በርካታ ጥረት ብናደረግም በ5 አመት ከ 2 ኪ.ሜ በላይ ሊሰራ አልተቻለም።
ነገር ግን እራሳችን ቆርጠን ስንገባባት 45 ኪ.ሜን የወንዝ ዳርቻዎች እና 1000 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ልማት በኢትዮዽያ ልጆች ዲዛይነርነት፣ አርክቴክትነት፣መሪነትና አስተባባሪነት ባሰብነዉና ባለምነዉ ልክ በ5 አመት ረጅም ጊዜ ዉስጥ ያልተቻለን በ7 ወራት ጊዜ ዉስጥ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ አሳክተናል ሲሉ ባሰፈሩት በመልዕክት ገልፀዋል።
ኢትዮዽያን በሁለንተናዊ መልኩ ለማበልፀግ ባላቸዉ ራዕይ ከጐናችን ያልተለዩትን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ፣የልማታችን ዋነኛ አጋሮች ሆናችሁ አብራችሁን የሰራሁ ባለሀብቶች ፣ አመራሮች ፣ ሰራተኞች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች፣ ማህበራት እንዲሁም የልማታችን ደጀን የሆናችሁ የከተማችንን ነዋሪ የላቀ ምስጋና ይሁን እላለዉ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።