20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የማንሰራራት ጉዞ ውጤት እየተመዘገበ ባለበት ወቅት የሚከበር መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት ህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ የሚከበረው 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መሪ ዕቅድ ላይ የአብይ ኮሚቴ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚህ ወቅት እንዳሉት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አንድነትና ወንድማማችነት የሚረጋገጥበት በዓል ነው።
የ2018 ዓ.ም የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የማንሰራራት ጉዞን የጀመረችበትና ውጤትም እየተመዘገበ ባለበት ወቅት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚመረቅበት እንዲሁም አገራዊ የምክክር ሂደቱ በተደራጀ አግባብ በሚጀመርበት ወቅት መከበሩም እንዲሁ በዓሉን ልዩ የሚያደርገው መሆኑን ጠቁመዋል።
በዓሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚከበር መሆኑን አንስተው፤ ይህም የክልሉን የልማት ስራዎች፣ ለመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት መነቃቃት የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በዓሉ በአገር ደረጃ በፌዴራል፣ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚከበር ሲሆን የማጠቃለያ መርሃ ግብር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ይከበራል።
በማሬ ቃጦ