በጄኔቫ ለ10 ቀናት የተካሄደው የፕላስቲክ ብክለት ድርድር ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ

You are currently viewing በጄኔቫ ለ10 ቀናት የተካሄደው የፕላስቲክ ብክለት ድርድር ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ

AMN- ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም

‎በጄኔቫ ለ10 ቀናት የተካሄደው 6ኛው የፕላስቲክ ብክለት ድርድር ያለ ስምምነት ተጠናቋል።

በፈረንጆቹ 2022 በተባበሩት መንግስታት (ተመድ) የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ስር በሴኔጋል ዳካር ሃሳቡ ቀርቦ በኡራጓይ የተጀመረው ድርድር፣ በተለያዩ ዓመታት 5 ጊዜ ቢካሄድም እስካሁን የጋራ ስምምነት ላይ ባለመደረሱ መቋጫውን አላገኘም።

የፕላስቲክን ከምርት እስከ አወጋገድ ያለውን ዑደት ለመቆጣጠር እና በአካባቢ እና በጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ታስቦ የተጀመረው ድርድር በፈረንጆቹ 2025 መቋጫውን ያገኛል በሚል እሳቤ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ለ10 ቀናት ቢካሄድም፤ አሁንም ከስምምነት አለመደረሱ በተሳታፊዎች ዘንድ ቅሬታን አጭሯል።

ላለመግባባቱም በመጨረሻው ቀን በረቂቅ ሃሳቡ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ረቂቅ ሃሳቡ በምርቶች ገደብ፣ የኬሚካል እና የተወገዱትን አያያዝ፣ የመልሶ መጠቀም እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን የመደገፍ ጉዳዮች ላይ ደካማ አቋምን የያዘ ነው በሚል በሀገራት መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል።

የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ከደካማ ስምምነት ይልቅ ስምምነት አለማድረግን የደገፉ ሲሆን፣ ስምምነቱን ከዳር ለማድረስ ቀጣይ ሂደቶች እንደሚኖሩ ይጠበቃል።

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review