ደቡብ ኮሪያ ወንጀልን ለመከላከል ያግዛሉ ያለቻቸውን የብርሃን ጨረር ፖሊሶች በሴኡል ሰው በሚበዛበት ጁዶንግ መናፈሻ አሰማርታለች።
ሆሎግራም የተባለ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በመናፈሻው ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እስከ 4፡00 ሰዓት የሚቆሙት ፖሊሶቹ፤ የ1 ሜትር ከ70 ሴንቲ ሜትር ቁመት ያላቸው ናቸው።
ሆሎግራሚካ በተባለ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የተሰሩት የጨረር ፖሊሶች፣ በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱ ነዋሪዎች የአእምሮ መረጋጋትን ለመፍጠር እና የስርአት አልበኝነትን ለመከላከል ታስበው የተዘጋጁ መሆናቸውን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
ከትክክለኛ የሰው ቁመና ጋር ተመሳሳይ ተደርገው የተሰሩት የብርሃን ጨረር ፖሊሶቹ፣ ባሳለፍነው ዓመት ጥቅምት ላይ ለሙከራ መሰማራታቸው ተዘግቧል።
እንደከተማዋ ሜትሮፖሊታን ፖሊስ ኤጀንሲ ከሆነም፣ የብርሃን ጨረር ፖሊሶቹ ከተሰማሩ ጀምሮ በመናፈሻው አካባቢ የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊቶች በ22 በመቶ ቀንሰዋል።
ምንም እንኳን ከነዚህ የጨረር ፖሊሶች ጎን ለጎን የቁጥጥር ካሜራዎች በስፍራው ያሉ ሲሆን፣ በድንገተኛ ጊዜያት ፈጥነው የሚደርሱ ፖሊሶች በአካባቢው መኖራቸውንም ዘገባው ጠቅሷል።
በሊያት ካሳሁን