አሌክሳንደር ኢዛክ በሊቨርፑል እንደሚፈለግ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ተጫዋቹ የዝውውር አማራጮችን አይቶ ለሌላ ክለብ መጫወት እንደሚፈልግ በድብቅ ሳይሆን አለም እንዲያውቀው አድርጎ በማህበራዊ ገፁ አሳውቋል፡፡
ኒውካስትል ዩናይትድም ባሳየው ፀባይ ደስተኛ እንዳልሆነ ተናግሯል፡፡ ውዝግቡ እልባት ሳያገኝ ቀናት እየነጎዱ የዝውውር መስኮቱ ሊዘጋ ተቃርቧል፡፡
የ25 ዓመቱ አጥቂ በዋነኛነት የሚፈለገው በዛሬው የኒውካስትል ዩናይትድ ተጋጣሚ ሊቨርፑል እንደሆነ በርካታ ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡
ቀዮቹ ስዊድናዊውን አጥቂ ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል 110 ሚሊየን ፓውንድ የተረጋገጠ ክፍያ ፤ ከተጫዋቹ ስኬት ጋር የተያያዘ ደግሞ 10 ሚሊየን ፓውንድ ለመጨመር ፍቃዳቸውን ቢያሳዩም በኒውካስትል ፊት ተነስተዋል፡፡
በተጫዋቹ የዝውውር አዙሪት ውስጥ አንደኛው ተዋናይ የሆነው ሊቨርፑል ምናልባት ዛሬ በሴንት ጀምስ ፓርክ የመረረ አቀባበል ሊደረግለት ይችላል፡፡
ጠንከራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የኢዛክ የዝውውር ወሬ ጋርዶታል፡፡ ቢሆንም ግን ጨዋታውን የሚመሩት ሳይመን ሁፐር ፊሽካ ከተሰማ በኋላ የሁሉም ትኩረት ጨዋታው ላይ መሆኑ አይቀርም፡፡
ሻምፒዮኑ ሊቨርፑል የውድድር ዓመቱን ቦርንማውዝን በማሸነፍ ጀምሯል፡፡ የመርሲሳይዱ ክለብ አሳማኝ ብቃት ባያሳይም ወሳኙን ሦስት ነጥብ ወስዷል፡፡
ቀዮቹ ዛሬ ፈታኙን ኒውካስትል ዩናይትድን ቢገጥሙም በሴንት ጀምስ ፓርክ ያላቸው ክብረወሰን በራስመተማመናቸውን ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡
ሊቨርፑል ወደ ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል ባደረጋቸው የመጨረሻ ስምንት ጉዙዎች ውጤታማ ነበር፡፡ በአምስቱ አሸንፎ በሦስቱ አቻ ተለያይቷል፡፡
በዝውውር መስኮቱ አስቸጋሪ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ኒውካስትል ዩናይትድ ከ2015 ጀምሮ ያላሸነፈው ሊቨርፑልን ለመርታት ምርጥ ብቃቱ ላይ መገኘት ይኖርበታል ፡፡
በሊቨርፑል በኩል ቅጣት ላይ የነበረው አማካዩ ርያን ግራቨንበርች ወደ ስብስቡ ሲመለስ ጉዳት የገጠመው አዲስ ፈራሚው ጀርሚ ፍሪምፖንግ በጨዋታው አይሳተፍም፡፡
በኒውካስትል ዩናይትድ በኩል ከጆ ዊሎክ ውጪ ሁሉም ተጫዋቾቻቸው ለጨዋታው ብቁ ናቸው ተብሏል፡፡
ሁለቱ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት በካራባኦ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ ነበር፡፡ ኒውካስትል ጨዋታውን 2ለ1 አሸንፎ ከ70 ዓመት በኋላ ዋንጫ ማንሳቱ ታወሳል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ