በጃፓን በጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ ስም መንገድ የመሰየም ሥነስርዓት በኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል የሚመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በተገኘበት በይፋ ተከናውኗል፡፡
መርሐ-ግብሩ የተካሄደውም በኢፌዲሪ ኤምባሲ አዘጋጅነት በጃፓን ዮኮሃማ እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮ-ጃፓን የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ፎረም ማጠቃለያ ላይ ነው፡፡
በሥነ ስርዓቱም የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ ሁነቱ በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።
“እውነተኛ ወዳጅነት ዘላለማዊ ሀብት ነው” የሚለውን የጃፓናውያንን ምሳሌ በመጥቀስም፣ ይህ አጋጣሚ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ትብብር የሚያመለክት አዲስ ምዕራፍ እንደሆነ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው ጀግኖች መካከል አንዱ ለሆነው ብሔራዊ ጀግና ክብር በመስጠታቸው ለጃፓን መንግስትና ህዝብ በተለይም ለካሳማ ከተማ ነዋሪዎችና አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።
በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ፣ የኢትዮጵያና የጃፓን ህዝብ ይህንን ዕለት ልዩ ቀን አድርጎ እንደሚያስበው ገልፀው፣ አዲሱ ትውልድም አትሌቱን እንዲያስታውስ ወሳኝ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
የካሳማ ከተማ ከንቲባ ያማጉቺ ሺንጁ በበኩላቸው፣ ይህ መንገድ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ጠቅሰዋል።
መንገዱ በ1964 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ አስደናቂ ድል በተቀዳጀው እና ዓለምን ያስደመመ ገድል በፈጸመው አበበ ቢቂላ ስም መሰየሙ፣ ጥልቅ ትርጉም ያለው መሆኑም ተገልጿል።
ይህ ድል ለኢትዮጵያ ትልቅ ኩራት ከማጎናፀፉም በላይ፣ ከጃፓን ህዝብ ጋር ዘላቂ የሆነ ግንኙነት መፍጠር እንዳስቻለ መመላከቱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።