የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ያዘጋጀው ሁለተኛው የንግድ ሳምንት ኤግዚቢሽን በኦሮሞ የባህል ማዕከል ተከፍቷል፡፡
ከነሐሴ 19 እስከ 21/2017 ዓ.ም በሚቆየው በዚህ ኤግዚቢሽ ላይ የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ቀርበዋል፡፡
”ሁሉን አቀፍ የንግድ ዕድገት ለብልጽግና ጉዞ ግብ” በሚል መሪ ሀሳብ በተከፈተው የኢትዮጵያን ይግዙ ኤግዚቢሽን ላይ ከሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች የመጡ አምራቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው ቀርበዋል።
ኤግዚቢሽኑን የከፈቱት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ገበያው እንዲረጋጋ፣ የኑሮ ውድነቱም እንዲቀንስ የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት መድረኮች ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል።

መድረኩ ተኪ ምርትን በማበረታታትና ወጪ ምርትን በማሳደግ ረገድ ትልቃ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ኃላፊ የሺ ጂማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሳምንቱ የኦሮሚያ ክልል የንግድ ሳምንት ተብሎ መሰየሙን ጠቅሰው፣ ክልሉን ከሌሎች ክልሎች ጋር በንግድ ለማስተሳሰርና ልምድ እንዲለዋወጡ አላማ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የሚመረቱ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በሚገባ ለማስተዋወቅ የሚያግዝ መድረክ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት።
በኤግዚቢሽኑ ላይ ከቀረቡት ለዓለም ገበያ ከሚቀርቡ የግብርናና የማዕድን ምርቶች መካከል የቁም ከብቶችን ጨምሮ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ማር እና ማሾ የተለያዩ የቦለቄ ዝርያዎች እና የአምቦ ድንጋይ ምርቶች የሚጠቀሱ ናቸው።
ለሀገር ውስጥ ገበያ ከሚቀርቡት ምርቶች ውስጥ ደግሞ የሰብልና የጥራጥሬ ምርቶች፣ ወተትና የወተት ተዋጽኦ፣ የስንዴ ዱቄት፣ የምግብ ዘይትና ሌሎች እሴት የተጨመረባቸው የፋብሪካ ውጤቶች ይጠቀሳሉ።
በምትኩ ተሾመ