ከ500 በላይ የተለያዩ የመኪና ዕቃዎችን ከ11 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ

You are currently viewing ከ500 በላይ የተለያዩ የመኪና ዕቃዎችን ከ11 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ

AMN – ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም

በጥናት ላይ በተመሰረት የኦፕሬሽን ስራ ከ500 በላይ የተለያዩ የመኪና ዕቃዎችን ከ11 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በከተማዋ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን መነሻ በማድረግ ተከታታይነት ያለው የጥናት፣ የክትትል፣ የምርመራና የኦፕሬሽን ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሚዲያ በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ ሦስትና ወረዳ ዘጠኝ ልዩ ቦታው ጌጃ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከተለያዩ ቦታዎች ተሰርቀው ለገበያ የሚቀርቡ የመኪና ዕቃዎች መኖራቸውን በተደረገው የጥናት ስራ መለየቱ ተገልጿል፡፡

የልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ተገቢውን የፍርድ ቤት የመበርበሪያና የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣት በተጠቀሱት ሁለት ወረዳዎች ከሌባ የሚገዙና የሚቀበሉ ግለሰቦች ላይ በጥናት በተለዩ መኖሪያ ቤቶቻቸውና የመኪና ዕቃ መሸጫ ሱቆቻቸው ውስጥ ባደረገው ብርበራና ፍተሻ 215 የጎን መስታወት (ፍሬቻ) ፣ 126 ፍሬቻ፣ 56 የፊት መብራት፣ 70 ጌጅ፣ 30 የመኪና ጌጥ፣ 6 ሳልቫትየ ክዳን፣ 17 የውስጥ ስፖኪዮ፣ 4 ቸርኬ፣ 5 ጎማ እና ሌሎች የመኪና ዕቃዎችን ከ11 ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እያጣራ መሆኑን ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ የማስፋት ተግባራትን በማከናወን ተጨማሪ ተጠርጣሪዎችንና ኤግዚቢቶችን ለመያዝ እየሰራ መሆኑን ፖሊስ ገልፆ የመኪና ዕቃ ተሰርቆብኛል የሚል አካል ልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመምጣት ዕቃውን መለየትና መረከብ እንደሚችልም አስታውቋል፡፡

ህብረተሰቡ መሰል የወንጀል ድርጊት በሚፈፀምበት ወቅት ከሌቦች ጋር በመደራደር የራሱን ንብረት ለመግዛት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለወንጀለኞች እውቅና መስጠት መሆኑን አውቆ ከድርጊቱ በመታቀብ በአቅራቢያ ለሚገኝ ፖሊስ ተገቢውን መረጃ በመስጠት በወንጀል ፈፃሚዎች ላይ ህጋዊ ርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ እንደሚገባው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review