ከትራምፕ የነጩ ቤት ቁጣ ያመለጡት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት

You are currently viewing ከትራምፕ የነጩ ቤት ቁጣ ያመለጡት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት

AMN – ነሔሴ 20/2017 ዓ.ም

አዲሱ የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሊ ጃማዩንግ ኋይት ሀውስ ሲደርሱ ትራምፕ በዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዘለንስኪ እና በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ላይ ያሳዩት አይነት ተቃውሞ እና ቁጣ እንደሚጠብቃቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

ይህ ስጋት እንዲፈጠር ያስቻለው ደግሞ ትራምፕ ከፕሬዚዳንቱ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ስለምትገኘው ሀገር ትሩዝ በተሰኘው ማህበራዊ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ሀሳብ ነው።

ግራ ዘመም ናቸው የሚባሉት የደቡብ ኮሪያው መሪ ሊ ጃማዩንግ፣ ከቻይና ጋር ጠንካራ ግንኙነትን ለመመስረት ማቀዳቸው በትራምፕ አስተዳደር ዘንድ ሌላ ጥያቄ ያስነሳባቸው ጉዳይ ነበር።

ከዚህ ባለፈም ትራምፕ ሀገሪቱ ለወታደራዊ ወጪ የምትበጅተው ገንዘብ በቂ አለመሆኑን እና በስፍራው በሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ጥበቃ ላይ ደህንነቷ የተንጠለጠለ ነው በሚል ይተቻሉ።

እነዚህ ሁሉ ቅራኔዎች ታዲያ የዘለንስኪ የኦቫል ኦፊስ ቆይታ በደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ላይ ሊደገም እንደሚችል ስጋትን ቀስቅሰዋል።

ይሁን እንጂ፣ ሊ ጃማዩንግ የተፈራውን ለማስቀረት የተጠቀሙት በፈገግታ የታጀበ የወዳጅነት አቀራረብ ትራምፕ ያሰቡትን እንዲተው ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ ቢቢሲ ዘግቧል።

መሪዎቹ የንግድ እና የመከላከያ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከርም ተስማምተዋል።

በሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ሰላም ማምጣት የሚችሉት ብቸኛ ሰው ትራምፕ እንደሆኑ የገለጹት ሊ ጃማዩንግ፣ ሰላም ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ሴዑል ድጋፏን እንደምታደርግ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር መገናኘት እና መወያየት እንደሚፈልጉም በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review