ኢትዮጵያ ከኮሎምቢያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሃብረቢ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ሰፊ የገበያ ዕድሎችና በርካታ የሰለጠነ የሰው ሀይል ያላት ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገር መሆኗንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እና የኮሎምቢያ የኢኮኖሚ እና ቢዝነስ ውይይት የሁለቱ ሀገራት የሥራ ኃላፊዎችና የኮሎምቢያ ባለሀብቶች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሃብረቢ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ እና ኮሎምቢያ የረጅም ዓመታት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በሌሎች ዘርፎች ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደምትሰራም ጠቁመዋል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን በመተግበር ለውጭ ኢንቨስተሮች ምቹ ምህዳር መፍጠሯን ጠቅሰዋል።
በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፎች ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳሏት መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኮሎምቢያ ምክትል የንግድ ሚኒስትር ሉዊስ ፊሊፔ ኩዊንቴሮ በበኩላቸው፥ ኮሎምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል