የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የስዊዘርላንድ አምባሳደር ታማራ ሞና እና የማልታ አምባሳደር ሮናልድ ሚካሌፍን አሰናብተዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ ሁለቱ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲጠናከር ተሰናባቾቹ አምባሳደሮች ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋና አቅርበዋል።
ፕሬዚዳንቱ በተለይም ከስዊዘርላንድ አምባሳደር ጋር በነበራቸው ውይይት ለበርካታ ጊዜ የዘለቀው የሀገራቱ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን አንስተዋል።
ግንኙነታቸው በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ደረጃ በሚደረጉ ይፋዊ ጉብኝቶችና የፖለቲካ ምክክሮች አጋርነቱ ይበልጥ እየጎለበተ መምጣቱ ተገልጿል።
በተመሳሳይ ማልታ በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ብትከፍትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር በትምህርትና በባህል ዘርፎች ጠንካራ አጋርነት መመስረት መቻሏ ተመላክቷል።

ፕሬዝዳት ታዬ እያደገ ያለው ግንኙነት በተለይ በኢኮኖሚ ዘርፍ ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ ማንሳታቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር አብርሃም መንግሥቱ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ተሰናባቿ የስዊዘርላንድ አምባሳደር ታማራ ሞና በቆይታቸው ስዊዘርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላት ጠቅሰው፥ ይህንን ለማጠናከር ውጤታማ ሥራዎች መስራታቸውን ተናግረዋል።
በንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱን ለማጠናከር በርካታ ዕድሎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በእነዚህ ዘርፎች በቀጣይ ይበልጥ እንደሚሰራባቸው አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ተሰናባቹ የማልታ አምባሳደር ሮናልድ ሚካሌፍ፤ማልታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ በመክፈት የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል አመርቂ ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም ሁለቱ ሀገራት ያሏቸውን ግንኙነቶች በኢኮኖሚ ዘርፍ እና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።