ዘንድሮ ለ71ኛ ጊዜ የሚከናወነው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሊግ ዙር እጣ ድልድል ምሽቱን በሞናኮ ይፋ ሆኗል።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የሚያዘጋጃቸውን ሁሉንም የክለብ ውድድር ዋንጫዎችን ያሸነፈው ብቸኛ ክለብ ቼልሲ የማስታወሺያ ሽልማት ተበርክቶለታል።
ዝላታን ኢብራሂሞቪች ደግሞ የ2025 የዩ ኤ ፋ የፕሬዝዳንት ሽልማት አሸናፊ ሆኗል። በቀድሞ የኤ ሲ ሚላን እና ሪያል ማድሪድ ኮከብ ብራዚላዊው ካካ እና ስዊድናዊው ታሪካዊ ተጫዋች ዝላታን ኢብራሂሞቪች መሪነት በወጣው ድልድል 36 ክለቦች ተሳታፊ ይሆናሉ። በእጣ ድልድሉ መሰረት በጉጉት የሚጠበቁ ጨዋታዎች በርክተው ታይተዋል።
አርሰናል ከባየርን ሙኒክ ፣ ኢንተር ሚላን እና አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች አጓጊ ናቸው። ፓሪሰን ዠርማ ባየርን ሙኒክ እና ባርሴሎና ጋር እንዲጫወት ተደልድሏል።

ማንችስተር ሲቲ ከ ሪያል ማድሪድ ፤ ሊቨርፑልም ከ ሪያል ማድሪድ ጋር ተጠባቂ ጨዋታ ያደርጋሉ። ቼልሲ በበኩሉ ከባርሰሎና እና ባየርን ሙኒክ ጋር የመጫወት ግዴታ ተጥሎበታል። በዚህ ዙር እያንዳንዱ ክለብ ስምንት ስምንት ጨዋታዎችን ያከናውናል።
ባለፈው ዓመት የተጀመረው አዲሱ ፎርማት ክለቦች በሚሰበስቡት ነጥብ መሰረት ከ1 እስከ 8 የሚጨርሱት ቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ያልፋሉ።
ከ9 እስከ 24 የሚጨርሱ ደግሞ እርስ በእርስ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አድርገው አሸናፊዎቹ ቀጣዩን ዙር ይቀላቀላሉ። ከ25 እስከ 36 የሚጨርሱ ክለቦች ከውድድሩ ይሰናበታሉ። በዘንድሮው ውድድር እንግሊዝ ስድስት ክለቦችን በማሳተፍ ቀዳሚውን ስፍራ ይዛለች። የ2025/26 የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በሃንጋሪ ቡዳፔስት ፑሽካሽ አሬና ይከናወናል።
በሸዋንግዛው ግርማ