በአፍሪካ ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት ለመፍጠርና ለቀጣናው ደህንነት መረጋገጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትር እና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ-ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሽዴ ገለጹ።
ኢትዮጵያ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን 50ኛው የከፍተኛ ባለሙያዎች፣ 25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ እና ስምንተኛው የመንግስትና የግሉ ዘርፍ የውይይት ፎረምን እያስተናገደች ነው። ዛሬ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ-ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን 25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መካሄድ ጀምሯል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የቦትስዋና ምክትል ፕሬዝዳንት ንዳባ ኒኮዚናቲ፣ የገንዘብ ሚኒስትር እና ኢትዮጵያ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ፕሬዝዳንት አህመድ ሽዴ፣ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ፋይክል ዚታ፣ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረን ጨምሮ ከተለያዩ አገሮች የመጡ የሥራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ታድመዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር እና የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ሚኒስትሮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መድረኩ ለሁሉም አባል አገሮችና ለቀጣናው ጠቃሚ ነው።
የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ማጭበርበርን እንዲሁም ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል ለሁሉም ኃላፊነት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን መከላከል የቀጣናውን ደህንነት በማረጋገጥ አስተማማኝ ኢንቨስትመንት መሳብ እንደሚቻል ተናግረዋል።
የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ማዕቀፍ ብዙ አገሮች ጥሩ እየሰሩ ቢሆንም ውስንነት ያለባቸውም እንዳሉ ተናግረዋል። በመሆኑም የቡድኑን ራዕይ ለማሳካት የህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመከላከል ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር የወንጀል ሰንሰለቱን መበጠስ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ የግሉንና የመንግስትን ትብብር በማሳደግ ቀጣናዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል። ኢትዮጵያ የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ጸረ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን ራዕይ እንዲሳካ በጋራ የመስራትና የመተባበር ስራዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግረዋል።