ሊቨርፑል ከ አርሰናል ቁጥሮች ምን ይነግሩናል?

You are currently viewing ሊቨርፑል ከ አርሰናል ቁጥሮች ምን ይነግሩናል?

AMN – ነሃሴ 25/2017 ዓ.ም

በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የፉክክር ደረጃቸው ከፍ ካሉ ጨዋታዎች አንዱ የሆነው የሊቨርፑል እና አርሰናል ፍልሚያ ሊጀምር ጥቂት ሰዓታት ብቻ ቀርተዋል።

ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ ግቦች ይዘንባሉ ቢባል ይቀላል። ከ2015/16 በኋላ ባደረጓቸው 20 ጨዋታዎች 78 ግቦች ተቆጥረዋል። በእነዚ 10 ዓመታት ውስጥ በሊጉ የትኛውም የእርስ በእርስ ግንኙነት ይህን ያህል ግብ አላስመለከተም።

ሊቨርፑል አርነ ስሎትን ካመጣ በኋላ ካደረጋቸው 40 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በ39ኙ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ቀዮቹ በእነዚህ ጨዋታዎች 93 ግብ አስመዝግበዋል። የአንፊልዱ ክለብ በመከላከሉ ግን ደከም ብሎ ታይቷል። ዘንድሮ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሰባት ግብ ቢያስቆጥም አራት ግቦች ተቆጥረውበታል።

የተከላካይ ክፍሉ ደከም ቢልም ለጊዜው የማጥቃት ሃይላቸው ውጤት ይዘው እንዲወጡ እያደረጋቸው ይገኛል። የበርካቶች ጥያቄ ግን እንደ አርሰናል አይነት ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ክለብ ሲገጥሙ እንዴት ይሆናሉ? የሚል ነው። አርሰናል በሁለት የመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታዎች ግብ አልተቆጠረበትም። 22 ሙከራዎች በተደረጉበት የኦልትራፎርዱ ጨዋታ ጭምር መረቡን አላስነካም።

ሌላው የመድፈኞቹ ጥንካሬ ከማዕዘን ምት በርካታ ግብ የማስቆጠር አቅማቸው ነው። ከ2023/24 የውድድር ዓመት ጀምሮ 33 ግቦችን አስቆጥረዋል። በዚህ ቁጥራዊ መረጃ ከአምስቱ ታላላቅ ሊጎች አርሰናል ቀዳሚው ክለብ ያደርገዋል። ሁለተኛ ደረጃ ከተቀመጡት ባየር ሊቨርኩሰን እና ቦሩሲያ ሞንቼግላድባህ በ10 ግብ ይበልጣል።

የሚካኤል አርቴታው ቡድን ዘንድሮም ይህን ጥንካሬውን አስቀጥሏል። ከመረብ ካሳረፏቸው ስድስት ግቦች ሦስቱ የተቆጠሩት ከመዕዘን በተሻገሩ ኳሶች ነው። ታይምስ ስፖርት ላይ የሚፅፈው አንጋፋው ጋዜጠኛ ማርቲን ሳሙኤል የአርሰናል በመከላከል አደረጃጀቱ መመካትን አልወደደውም። መድፈኞቹ ከሊቨርፑል ጋር አንገት ለአንገት መተናነቅ ካለባቸው በርካታ ግብ አስቆጥረው ማሳየት አለባቸው ባይ ነው።

የማርቲን ሳሙኤል መከራከሪያ “ባርሰሎና ሀቪየር ማሸራኖን ተከላካይ አድርጎ በርካታ ዋንጫዎችን ሰብስቧል፤ ምክንያቱም ተጋጣሚ ቡድኖች ባርሳን ለማጥቃት ሳይሆን ለመከላከል ስለሚያስቡ ነው” ብሏል። ሚካኤል አርቴታ በዚህ ሃሳብ የሚስማማ አይመስልም ምክንያቱም አርሰናልን ከተረከበ በኋላ አብዛኛውን በጀቱን ፈሰስ ያደረገው ተከላካዮች ላይ እንደሆነ ታይቷል።

አርሰናል በሊጉ በሁለት ጨዋታ ሁለት ግብ ያስቆጠረው ሁጎ ኢኪቲኬ ላይ አይኑን መጣሉ አይቀርም። የበለጠ ትኩረት ማድረግ ያለባቸው ግን ሞሐመድ ሳላህ ላይ ይመስላል። ግብፃዊው ኮከብ አርሰናል ላይ 10 ግቦችን አስቆጥሯል። ሁለቱ ክለቦች ሲገናኙ በርካታ ግብ በማስቆጠር ቀዳሚው ተጫዋች 11 ግብ ያለው ሮቢ ፋውለር እንደሆነ የታሪክ መዝገባቸው ያሳያል።

ትራንስፈር ማርኬት ድረ ገፅ እንዳወጣው ቁጥራዊ መረጃ ሁለቱ የፕሪምየር ሊጉ ሃያላን 235 ጊዜ ተጫውተዋል። ቀዮቹ 89 መድፈኞቹ ደግሞ 81 ጊዜ ድል አድርገዋል። 63ቱን ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ሊቨርፑል የዛሬ ተጋጣሚው ላይ 357 ግቦችን ሲያስቆጥር ፤ አርሰናል 324 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል። እንዲህ በግብ የሚያንበሸብሸው የሁለቱ ክለቦች ግንኙነት ዛሬስ ምን ያስመለክተናል? ጨዋታው ምሽት 12:30 ላይ በአንፊልድ ይጀምራል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review