AMN – ነሃሴ 26/2014 ዓ.ም
ዓባይ የዘመናት ቁጭት፤ ብሶት እና የእንጉርጉሮ ምንጭ ሆኖ ትውልድን እየታዘበ እንዲሁ ሲፈስ ኖሯል።
ኢትዮጵያ ከምድሯ በፈለቀው የዓባይ ወንዝ ሳትጠቀም የበይ ተመልካች ሆና ሃብቷ በደጇፏ እያለፈ ዘመናትን በዝምታ ስትመለከት ቆይታለች፡፡ ይህንን የብሶት ዘመን ለመቋጨት ቆርጠው የተነሱ ኢትዮጵያዊያንም በጉባ ሰማይ ስር አዲስ ታሪክን ጽፈዋል። ዓባይ ከባከነ ጉዞው አርፎ ጉባ ላይ ሃይልም፤ ሃይቅም ሆኖ አንድነትንና ይቻላልን አስመስክሯል፡፡
ይህን የዘመናት ጥያቄ የመመለሱ ስራ እንዲሁ በቀላሉ የተገኘ ሳይሆን፤ በርካታ እልህ አስጨራሽ ሂደቶች የታለፉበት ነው ። የታላቁ የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት እጅግ ውስብስብና በፈተናዎች የታጠረ ነበር። ይህንን መቋቋም ደግሞ በሳል የአመራር ብቃትንና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ነበር፡፡ በፈተና ውስጥ ታልፎ ግን አሁን ላይ ለውጤት በቅቷል ። ዛሬ ላይ ህዳሴ ግድብ ብቻ አይደለም፤ ሌሎች ህዳሴዎችን ለመፍጠር የሚያስችል ትልምም ጭምር እንጂ። ግድቡ የአዲስ መንገድ ጅማሮ፣ የድል መስመር ቀያሽ፣ ህብርን በተግባር ያጋመደ የለውጥ ፋና ወጊ ሆኖ በከፍታ ማማ ላይ እንዲታይ የለውጡ አመራር ሚና ትልቅ ነበር ።
የለውጡ መንግስት ግደቡ ገጥሞት የነበረውን የግንባታ መጓተት፣ የአሰራር ብልሽቶች እና ሌሎች መሰረታዊ ችግሮችን በመፍታትና የሚያጋይሙ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን በመቋቋም ለህዝብ የገባውን ቃል ወደ ተግባር በመቀየር በህዳሴ ግድቡም ዳግም አስመስክሯል። ወትሮም ቢሆን “ድር ቢያብር….” በሚል ብሂል የሚታወቁት ኢትዮጵያዊያን እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ ህዳሴ ግደቡ ላይም ያለ ልዩነት ከመንግስት ጎን በመቆም አሁንም ለመላው ጥቁር ህዝቦች አርአያ የሆነውን የህዳሴ ግድብ ትርጉሙ ከግድብ በላይ መሆን ማሳየት ችለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባ ታላቁ የህዳሴ ግድብ መገኛ ከትመው “ የኢትዮጰያ የማንሰራራት ጅማሮ፣ የደም ጠብታ፣ የላብ ጠብታ ፣ የዕንባ ጠብታ፣ የውሀ ጠብታ ድምር ውጤት መሆኑን ይህ ግድብ ህያው ምልክት ሆኖ ለትውልድ ሲመሰክር ይኖራል” ማለታቸው ይታወሳል። በዚህ መሰረት ለቀጣይ ትውልድ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ተጋድሎ የሚዘክር ሀውልት በጉባ ሰማይ ስር ቆሟል ።
ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልእክት መነሻ የሚጋሩት ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ህዳሴ ግድብ ከግብ የደረሰው በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በወንድሞቻችን አጥንት እና ደም ጭምር ነው ሲሉም የሀሳቡን ጥልቀት ከ ኤ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።

ኢትዮጰያን ለዘመናት በትውልድ ቅብብሎሽ ማፅናት የተቻለው በላብ፣ በደም፣ በእንባ መሆኑን ከሚመሩት መስሪያ ቤት ጋር አቆራኝተው አጫውተውናል።
በአባይ ወንዝ ላይ የነበረው ኢ-ፍትሀዊ የሆኑ ጉዳዮች የቀድሞ እናቶች እና አባቶቻችን ሲቆጩበት እንደነበር፤ ይህንንም ቁጭታቸው ሲንከባለል ቆይቶ በ2003 ዓ.ም መሰረት መጣሉ ይታወሳል ።
በወንዙ አጠቃቀም ዙሪያ የነበሩ ስምምነቶች እና ህጎችም ኢትዮጰያን ባዳ ያደረጉ እንደነበሩ አስታውሰዋል። ይህም ለዘመናት አስተሳሰባችን እና እጃችን አስሮ ቆይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ በቀደመው ትውልድ ዓባይን የመገደብ ተግባር ባይሳካላቸውም ራዕያቸውን ለትውልድ በማስተላለፋቸው የአሁኑ ትውልድ ህልማቸውን ማሳካት መቻሉን ነው የጠቆሙት ።
የዘመናት እና የትውልድ ህልም የነበረው ይህ ግድብ በበርካታ ውጣ ውረዶች ታልፎ ትውልድ ዋጋ ከፍሎበት ሀብት አውጥቶ ፣ የተደከመበት እና የተሄደበት ርቀት የደምና የላብ ውጤታችን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
መስዋዕትነት ትርጉሙ በየአውዱ ነው ያሉት ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ለግድቡ ዛሬ ላይ እዚህ መድረስ ብዙ ኢትዮጵያውያን መስዋዕት መክፈላቸውን አስረድተዋል። በመሆኑም በህዳሴ ግድብ የቆመው ላብን፣ ደምን፣ እንባን እና ውሀን የሚገልፀው ሀውልት ይህንን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ሀውልቱ የዚህ ዘመን ትውልድ ለቀጣዩ ትውልድ የሰራውን ስራ የሚዘክርም የሚያስታውስ ነው። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከዘመናት አልፎ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ከግድብ በላይ ትርጉም ያለው የዘመኑ የታሪክ ማስታወሻ እና መታሰቢያ ጭምር እንደሆነም ገልፀዋል። በመሆኑም ይህ በግድቡ የቆመው ሀውልት ትውልዱ በዘመኑ ላስቀመጠው አሻራ የሚዘክር እና ከዚህ የላቀ ህዳሴዎችን መገንባትና መስራት እንደሚቻል የሚያነሳሳ ነው ብለዋል ።
በህዳሴ ግድብ የታየው የይቻላል መንፈስ እና የአንድነት ትብብር በቀጣይ የኢትዮጰያ የከፍታ ዘመን የሚያመላክትና አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚቻል በሌሎች ዘርፎች ያመላከተ ነው ሲሉ ነው የተናገሩት ፡፡
በሔለን ተስፋዬ