ሀገሪቱ ለዘመናት ካንቀላፋችበት በመንቃት ላይ በመሆኗ ሀይቁን ንጋት ግዱቡንም ህዳሴ ብለን ጠርተነዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባ “የኩስመና ታሪክ ማብቂያ” በሚል ርዕስ ቆይታ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በመገኘት ስለ ግድቡ አጠቃላይ እና አሁን ላይ የደረሰበትን ሁኔታ በተመለከተ ከማህበራዊ ጉዳይ አማካሪያቸው ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጋር ነው ቆይታውን ያደረጉት።
ግድቡን ተንተርሶ የተሰራው ግዙፍ ሀይቅ በኢትዮጵያም ሆነ በአህጉሪቱ 74 ትሪሊየን ሊትር ውሃ በማከማቸት ትልቁ እንደሆነ አንስተዋል።
በግድቡ ዙሪያ የተሰራው ሰው ሰራሽ ሀይቅ የበርካቶች የእውቀት፣ የክህሎት፣ የመስዋዕትነትና ሀብት ድምር ውጤት የያዘ እንደመሆኑ የወል ስም ሊሰጠው እንደሚገባም የሌሎች ሀገራት ተሞክሮን አያይዘው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለበርካታ አመታት ያላትን እምቅ ሀብት በአግባቡ ሳትጠቀም መቆየቷን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ ጠለቅ ብላ ማየት እንድትችል ከአንቀላፋችበት መንቃቷን የምታበስርበት የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ እንደመሆኗ ሀይቁን “ንጋት” በሚል ስም ሊጠራ እንደሚገባም አብራርተዋል።

“ንጋት” ማለት ጎህ ሲቀድ፣ረጅሙ ጨለማ አብቅቶ የብርሃን ፍንጣቂ ሲጀምር ያለው ጊዜ እንደመሆኑ የሠው ልጅም ከጠለቀው የእንቅልፍ ስሜት በመውጣት የሚነቃበት ለዓላማው ዝግጁ የሚሆንበት ወሳኝ ሰዓት መሆኑን አብራርተዋል።
አሁን ለኢትዮጵያ የነጋበት ምሽቱም ያበቃበት ጊዜ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ንጋቱ” ከፊቲችን ላሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች የምንነሳበት እንደመሆኑ ከፊታችን ያለ መልካም ስራ የሚጀመርበት የብርሃን ወቅት መምጣቱን በጉልህ ያሳያል ብለዋል።
በመሆኑም ሀይቁን ንጋት ግዱቡንም ህዳሴ ብለን ጠርተነዋል ሲሉ ገልፀዋል
ግድቡ በየአመቱ ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢን በማስገኘት በስድስት አመታት ውስጥም ወጪውን በመመለስ የኢትዮጵያን ከፍታ ያበስራል ብለዋል።
የንጋት ሀይቅና የህዳሴ ግድብ ባለቤት የሆነው መላው የኢትዮጵያ ህዝብና የሀገሪቱ ወዳጆች ትክክለኛውን ታሪክ ለትውልድ እንዲያስተላልፉ፣ በመደመር ስሜት እጅ ለእጅ በመያያዝ ለኢትዮጵያ ብልፅግና በጋራ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በሩቁ ከዓለምነው ህልማችን ለመድረስ ዓይናችንን ለአፍታ ባለመንቀል ያጣነውን መልሰን ቁጭታችንንም በስራ አርመን ፀንታ የምትቆም ሀገር ለትውልድ ስራ ለመስራት እንፅና ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመኑን በመዋጀት በኢትዮጵያ ጥቅም የማንደራደር ብቻም ሳይሆን ድሉ ቀጣይነት ያለው ብቻም ሳይሆን ፍሬውን የምንቀምስበት ነው ብለዋል።
ድሉ የሀገሬው ህዝብ ብቻም ሳይሆን የቀጠናው ሀገራትን ጨምሮ ለግብፅም ሲሳይ በመሆኑ በጋራ የማደግና የመበልፀግ ማሳያ በመሆኑ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
በሚካኤል ህሩይ