ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ በታዳሽ ኃይል አጠቃቀም እና ከተሞችን በማዘመን ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰዷን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ተናገሩ፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተዘጋጀው የዓለም የአየር ንብረት ሳምንት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
በመርሐ-ግብሩ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ስላሴ፣ ኢትዮጵያ በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል እና ምድርን አረንጓዴ በማላበስ ለየአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ሰጥታለች ብለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ታዳሽ ኃይልን ወደ ስራ በማስገባት እንዲሁም የከተሞችን ዘመናዊ መሰረተ ልማት ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር የዓለም የጋራ ችግር ለሆነው የአየር ንብረት ለውጥ በተግባር ምላሽ መስጠቷን ጠቅሰዋል፡፡
አፍሪካዊያን ፀጋቸውን በመለየት በተግባር ወደ ስራ መግባት እና የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ችግር መፍታት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ኢትዮጵያ ልምድ እና ተሞክሮዎቿን ለማጋራት ዝግጁ ናት ብለዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ችግር የጋራ ጉዳትን የሚያስከትል፤ የጋራ ምላሽንም የሚሻ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፡ ዓለም ችግሩን ለመፍታት በጋራ ይቆም ዘንድም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ ሳምንቱ ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ስላሴን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሀመድ አሊ የሱፍ እና የዓለም ሀገራት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በተመስገን ይመር