ህዳሴ – በልበ ብርሀኑ አንደበት

You are currently viewing ህዳሴ – በልበ ብርሀኑ አንደበት

AMN – ነሐሴ 28/2ዐ17 ዓ/ም

‎” አቅም ኖሮኝ ባልሆን ለተኩሱ
‎ወረቀትን አዋድጄ ከእርሳሱ
‎እዋጋለሁ ድንቁርናን አጥብቄ
‎ለነገ ብርሀን ሰላምን ናፍቄ”………… የሚል ስንኝ የቋጠረው መምህሩ ለአገራችሁ ምን ሰራችሁ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በሚል ግጥም መደርደሩን ልበ ብርሃኑ ጋዜጠኛ ያስረዳል።

‎የአይነ ስውራን ማደሪያ ትምህርት ቤት ሳለ መምህራኖቻቸው ለአገራችሁ ምን አደረጋችሁ ለሚለው ጥያቄ ህዳሴ ግድብ መልስ እንደሆነው አይነ ስውሩ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ሀብታሙ ባንታየሁ ያስረዳል። “አካል ጉዳተኛ ነኝ ብዬ ሳላስብ ለሀገሬ ህልም እውን መሆንና መሳካት የአቅሙን እና የድርሻውን መወጣቱን ለመምህሩ መግለፁን ተናግሯል።

‎ሁሉም አካል ጉዳተኛ በየፊናው ለግድቡ አዋጥቶ ለዛሬ ስኬት በቅቷል የሚለው ወጣቱ፣ የጋራ ህልማችን መሳካቱን፣ የጋራ ደስታችን መጎምራቱን ነው መግለፅ የምችለው ይላል።
‎ለልብ ስንቅ ለህሊና ምግብ ሀሳብ ይዞ እንደሚቀሳቀስ የሚገልፀው ባለ ልበ ብርሃኑ ጋዜጠኛ፣ ለሀገርህ ምን አደረክ ለሚለው ጥያቄ ዳግም አድዋን መውለዱን፣ ህዳሴን ማቆሙን ወይም መትከሉን የምናገርበት ሞራል ላይ እገኛለሁ ሲል አብራርቷል። ስለ ህዳሴ ግድብ ሲያስረዳ ፣ህልማችን እውን የሆነበት ፣ አላማችን ከግብ የደረሰበት ፣በጥረታችን ፍሬውን ያየንበት ሲል በልበ ሙሉነት ይገልፃል ።


‎የህዳሴ ግድቡን በምናቡ መሳሉን ፣ አንድነትን እና ህብረትን የሚዘክርበት የምንሰብክበት በማለትም ያስረዳል። ይህንን ደግሞ ” በመኖር እና በመሆን ራሱን ሲያርቅ እና ሲገዛ አባይን ከመሳል አልፎ ሆንኩት “በማለት ያስረዳል። የሀገሩን ገፅታ የለየበት በታላቁ ህዳሴ ግድብ መልክ እንደሆነ ጋዜጠኛው ይናገራል። ‎”ህዳሴን ሰፌድ ቢሆን፣ ግድቡን ለመስራት የተሰባሰቡ እጆች ደግሞ ሰበዝ ቢሆኑ የሁሉም መጋመድና ማበር የሚያሳየው የዛሬ ውጤቱን መሆኑን ነው የገለፀው።

‎የህብረታችን እና የአንድነታችን ውጤት መሆኑን ፣ ህዳሴ በዚህና በሌሎች ምክንያት ገፀ ብዙ ነው ሲል ሀብታሙ ይናገራል። በስነ ፅሁፍ ሙያው ስለ ህዳሴ ሲያስረዳ፣ ህዳሴ ግድብ አባይ ወንዝን በተመለከተ የተዜሙ ሙዚቃዎች ቁጭት እና ብሶት የወለደው ወይም የሞላበት ነበር በማለት ይገልፃል ። ‎የፍቅር አስከ መቃብር ልብ ወለድን ለአብነት ያነሳው ባለ ልበ ብርሃኑ ጋዜጠኛ፤ አባይ በረሀ ላይ የሞተውን በዛብህን ምሳሌ አድርጎ ትርጓሜ ሰጥቶታል።

‎አባይ በረሀ ላይ በዛብህን ለሞት ያበቁት ሽፍቶች የአባይ በተለይ ህዳሴ እንዳይገደብ ምክንያት የሆኑ የሞከሩትን እንደሚያሳይ የገለፀው ወጣቱ፣ ግድቡ ለስኬት እንዳይደርስ እቅፋት የሆኑትን አካላት ይመስላቸዋል ይላል ።

‎ያም ሆኖ ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ከአባይ ግርጌ ጎሀ ፅዮን ጥርኝ አፈር ያቋደሳቸውን በዛብህ፣ ሰብለ ወንጌል እና ጉዱ ካሳ በአንድ መካነ መቃብር ላይ መካተታቸው ሚስጥር ሰላማችን፣ ፍቅራችንና አንድነታችን ተጠቅመን ከጉባ ሰማይ ስር ያቆምነውን ህዳሴ ግድባችንን ያሳያል ብለዋል። ይህ ሚስጥር በስነ ፁሁፍ ሙያው ሳላነሳው ቀርቼ አላውቅም የሚለው ጋዜጠኛ ደራሲ ሀብታሙ፤ ለቀሪውም የምዘክረው የምነግረውም ይህንኑ ነው ብለዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ግዜያት ሳልሳዊ አድዋን እንደምንወልድ እምነቴ ነውም ብልዋል። ዳግማዊ አድዋን ስንወልድ በዚሁ ረክተን ብቻ እንድንቆም ብቻ ሳይሆን፣ ሳልሳዊ አድዋችንን እንድንገነባ ፣ እንድንፀንስ ፣ እንድንወልድ ካሁኑ በበለጠ ሀላፊነት የሚያሸክም እንጂ በዚሁ ረክተን እንድንቆም የሚያደርግ አይደለም በማለት አስረድቷል።

የመረዳት አቅማችን በተሳለው ልክ ህዳሴ ግድባችንን እናገዝፈዋለን ያለው ጋዜጠኛ ሀብታሙ ፣ ያልገባው ሊያቀለው ይችላል ካለ በኃላ “በምናብ አሳሳሉ በእዝነ ልቦና አደማመጡ ባይነህሊና አመለካከቱ ይወሰናል ።

‎ለምሳሌ በታሪክ እና በስነ-ፅሁፍም የዘገበውን አንድ ሀሳብ ሲገልፅ፣ የመንግስት ሰራተኛ ሆኖ ከደሞዙ ከማዋጣቱ በተጨማሪ ተማሪ እናቱ ከመቀነታቸው ፈተው ሁለት ብር እንዲያዋጣ ማድረጋቸውን ያስታውሳል። ግድቡ ለስኬት እንዲበቃ አለፍ ሲልም በፀሎትም ሀሳብ ያዋጣበት መሆኑን ጠቅሶ፣ ግድቡ እዚህ በመድረሱ ኩራት ይሰማኛል ብሏል።

‎ ከዚህ በተጨማሪ ህዳሴ ግድብ እንዲሰምር አሉባልታና ወሬዎችን ባለመስማት ባለማናፈስ እንዲሁም፣ ግድቡን ወደ ኃላ የሚጎትቱ ተግዳሮቶችን በማረቅ እና እርምት በመስጠት ሀሳብ ማዋጣቱን ተናግሯል። ለአዲስ አመት ዋዜማ ስለምንገኝ በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግሉ ያለው እቅድ እና ተስፋ ትልቅ መሆኑን ተናግሯል።

‎በሔለን ተስፋዬ

#GERD

#Ethiopia

#AMN

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review