የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫዎች ወደከተማዋ የሚገቡ፣ ከከተማዋ የሚወጡና በከተማዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች፣ ሚኒባሶችና አነስተኛ ሽፍን መኪኖች ላይ የመኪና ኦፕሬሽን ስራዎች እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
ቢሮው እያካሄደ ያለው የመኪና ኦፕሬሽን ስራ ተሽከርካሪዎቹ ጭነው የሚንቀሳቀሱት ልዩ ልዩ ሸቀጦች፣ ምርቶችና የኮንስትራክሽን ግብአቶች በህጋዊ ግብይት በደረሰኝ የተፈፀሙ ስለመሆናቸው ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑም ቢሮው ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል በላከው መረጃ ተገልጿል፡፡
በአንድ ሳምንት በተካሄዱ የቁጥጥር ስራዎች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 11 ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 4 ፣ በአቃቂ ቃሊቲ 5 ፣ በለሚ ኩራ 7 እንዲሁም በጉለሌ 7 ተሽከርካሪዎች ዕለታዊ ደረሰኝ ሳይዙ በከተማዋ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተው አስተዳደራዊ የቅጣት እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ለጫኑት እያንዳንዱ ዕቃም ደረሰኝ እንዲቆርጡ መደረጋቸው ታውቋል፡፡
በከተማዋ ጭነት የጫኑ ማንኛውም አይነት ተሽከርካሪዎች፣ ተሳቢዎች፣ ሚኒባሶች እና ሽፍን መኪኖች ለጫኑት እቃ ዕለታዊ ደረሰኝ የተቆረጠበት መረጃ ስለመያዛቸው የማረጋገጥ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑም ተመላክቷል፡፡
ቢሮው ትልልቅም ይሁኑ ትንንሽ መኪኖች እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከከተማው ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀት ደረሰኝ ስለመያዛቸው የማረጋገጥና ያልያዙት ላይ አስተዳደራዊ ቅጣት በመውሰድ ለእያንዳንዱ ለጫኑት እቃ ደረሰኝ እንዲቆርጡ እየተደረገ እንደሆነ ቢሮው ገልጿል፡፡
ማንኛውም የተሽከርካሪ ባለቤትና አሽከርካሪ እንዲሁም ነጋዴ በመኪና ላይ ጭኖ ለሚያንቀሳቅሰው ማነኛውም ምርት በዕለቱ የተቆረጠ ደረሰኝ የመያዝና ለከተማው የገቢዎች ቢሮ የቁጥጥር ሰራተኞች የማሳየት ሀላፊነት እንዳለበት ቢሮው አሳስቧል።