ተፈጥሮን ከቴክኖሎጂ ያሰባጠረችው ሲንጋፖር

You are currently viewing ተፈጥሮን ከቴክኖሎጂ ያሰባጠረችው ሲንጋፖር

AMN- ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም

አለም እያደገች እና እየዘመነች ስትመጣ ለተፈጥሮ የምትሰጠው ቦታ እና ትኩረት እየቀነሰ በምትኩ የህንጻ እና የብረት ቁልል እየበረከተ እንደመጣ ተፈጥሮ የሚገዳቸው ሰዎች የሚያነሱት የነቀፌታ ሀሳብ ነው።

ትንሿ የደሴት ላይ ሀገር ሲንጋፖር ግን ይህ ያልተጣላባት ተፈጥሮን ከቴክኖሎጂ ጽዳትን ከዘመናዊነት ጋር አጣምሮ ለመጓዝ እንቅፋት ያልገጠማት ሀገር ሆና በምሳሌነት ትጠቀሳለች።

እ.ኤ.አ ከ1963 በፊት በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበረችው ሲንጋፖር፣ ሀገር ሆና በራሷ ለመቆም ብዙ ፈተናዎችን አልፋለች።

ሀገሪቷ ከቅኝ ግዛት ማብቃት በኋላ ከማሌዢያ ፌዴሬሽን ተገንጥላ ሀገር ሆና ስትመሰረት የሲንጋፖር አባት በመባል የሚታወቁት ሊ ኩዋን ዬው መሪነቱን ተረከበ።

በዚህ ወቅት ሶስት ሚሊዮን ሕዝብ ሥራ አጥ፣ ሁለት ሦስተኛው ሕዝብም በሀገሪቷ ጥጋ ጥግ የሚኖር ስልጣኔ በወጉ ያልዘለቀው ህዝብ ነበር።

የጽዳት ጉድለት፣ የተሟላ መሠረተ ልማት አለመኖር፣ የብቁ ውሃ አቅርቦትና የተፈጥሮ ሀብት ውስንነት የአዲሲቷ ሀገር እራስ ምታቶች ነበሩ።

የወቅቱ መሪ ሊ ኩዋን ዬው ሀገራቸው ዛሬ ላይ የምትታወቅበትን ጽዱ፣ በቴክኖሎጂ የተራቀቀች፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ጽዳት በዓለም አቀፍ ደረጃ ምሳሌ የሆነች ሀገርን እውን ለማድረግ መሰረት የጣሉ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።

ይህን ተከትሎም ሀገሪቷ ከተመሰረተች ከ7 አመታት በኋላ ከእርሷ በምስረታም በኢኮኖሚ አቅምም ከሚልቁት ከደቡብ ኮርያ፣ ታይዋን እና ሆንግ ኮንግ ጋር መፎካከር ጀመረች።

እ.ኤ.አ በ1965 የሲንጋፖር ያልተጣራ የሀገር ውስጥ ምርት ገቢ በነፍስ ወከፍ 500 ዶላር ብቻ የነበረ ሲሆን፤ በ1991 የሲንጋፖር ያልተጣራ የሀገር ውስጥ ምርት ገቢ በነፍስ ወከፍ 14,500 ዶላር መሆን ቻለ።

አሁናዊ ቁጥራዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በደቡብ ምስራቅ እስያ የምትገኝው ትንሿ ሀገር 721.5 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት እና 5.7 ሚሊዮን የሚጠጋ የህዝብ ብዛት አላት።

በውስጧ ብዙ አረንጓዴ ቦታዎች እና በጥሩ ሁኔታ የተጠበቁ መናፈሻዎች ስላሏት “የአትክልት ከተማ” ተብላም ትጠራለች።

ተፈጥሮን ከከተማ ልማት፣ ጽዱ እና አረንጎዴነትን በምስረታዋ ውስጥ ለማካተት ከፍተኛ ጥረት ያደረገችበት መንገድ በብዙ አድናቆትን አትርፎላታል ።

በተፈጥሮ አጠባበቅ፣ በጽዳት እና በቴክኖሎጂ ስመጥር የሆነችው ሲንጋፖር፣ እዚህ ለመድረሷ የተለያዩ የህዝብ ማንቂያዎችን እና ህጎችን ተግባራዊ አድርጋለች።

በንጽህና እና በጥሩ ሁኔታ በተጠበቁ አረንጓዴ ቦታዎቿ የምትጠቀሰው ሀገር በቆሻሻ አያያዝ፣ በዘላቂ ልማት እና በአካባቢ ጥበቃ ጥብቅ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ታደርጋለች።

በሲንጋፖር በዶክተር ትዕዛዝ ለሕክምና ዓላማ ካልሆነ በስተቀር ማስቲካ ማኘክም ሆነ መሸጥ አይቻልም። መንገድ ላይ ምራቅ መትፋት፣ የሲጋራ ቁራጮችን፣ የላስቲክ ኮዳዎችን፣ ቆርቆሮዎችን፣ የከረሜላ መጠቅለያዎችንም ሆነ ሌሎች ትናንሽ ቆሻሻዎችን መጣልም ከፍተኛ ቅጣት ያስከትላል።

ሲንጋፖር ዝቅተኛ የወንጀል መጠን ከሚፈጸምባቸው ከዓለም ደህንነታቸው የተጠበቀ ከተሞች አንዷ እንደሆነች ይነገርላታል።

በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ የሆነውን የሲንጋፖር ዕፅዋት መናፈሻን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፓርኮች፣ መናፈሻዎች እና የተፈጥሮ ጥበቃዎች ስራ ውጤት ነች።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review