ህመሟ ሳይበግራት ሀገሯን ከፍ ያደረገቸው አትሌት

You are currently viewing ህመሟ ሳይበግራት ሀገሯን ከፍ ያደረገቸው አትሌት

AMN – ጳጉሜ 1/2017 ዓ.ም

ሩጫ ለኢትዮጵያ ሁሉ ነገር ነው፤ ምን ያህል እንዳከበርነው ቢያጠያይቅም የብዙ መልኮቻችንን የገለጠ ነው። እንደ ህዝብ ምን ያህል የፀናን ፣ ፈተናን የመወጣት አቅማችን እና ገድል የመስራት ቁርጠኝነታችንን በስፖርቱ ዘርፍ በተለይም ደግሞ በሩጫ በተለያየ መድረኮች ገልፀን አሳይተናል።

ከአበበ ቢቂላ እስከ ሀይሌ ገብረ ስላሴ ከደራርቱ ቱሉ እስከ ጥሩነሽ ዲባባ የጀግንነት መልኮቻችንን የተገለጡበት መድረኮች ብዙ ናቸው፡፡ እኤአ 2007 የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ደምቀው የመታየት ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነበረች። ሦስት ወርቅ አንድ ብር በማምጣት ከአለም አገራተኛ ከአፍሪካ ቀዳሚ የነበረችው ኬንያን ተከትላ በማጠናቀቅ ግምቱን እውን አድርጋለች።

በኦሳካ ከተገኙት ሦስት ወርቆች ጥሩነሽ ዲባባ ያሳካችው የ10ሺ ሜትሩ የተለየ ትርጉም የተሰጠው ፅናት ካለ ምንም ነገርን ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ የሆነ ነው። ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ግምቶች ሁሉ ኢትዮጵያዊቷ እንቁ ላይ ያተኮሩ ነበሩ፤ በርካቶች ድል እንደሚቀናት አልተጠራጠሩም ነበር። በወቅቱ 22ኛ አመቷን ለመድፈን ሁለት ወር የቀራት ጥሩነሽ ዲባባ ብቃቷን ለዓለም ያስተዋወቀችው ኦሳካ ከመድረሷ ሦስት ዓመታት በፊት ነበር።

ብዙዎች ባዩት ነገር ተደምመው ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአትሌትክሱ ዘርፍ ካስጠሯት አትሌቶች በተጨማሪ ሌላ ጀግና እንዳፈራች መስክረዋል። ገና ከጅምሩ ማሸነፏን ያወቀች የምትመስለው ጥሩነሽ ዲባባ፤ ውድድሩን ከጀመረች በኃላ ክፉኛ የሆድ ህመም አጋጠማት። ሆዷን እያሻሸች ስትሮጥ በተደጋጋሚ የካሜራ እያታ ውስጥ ገብታም ነበር። ህመሟን ችላ በመሮጥ ላይ የነበረችው ጥሩነሽ ዙሩ እየከረረ ሲመጣ አቅም ያጣች የመጣች ትመስል ነበረ። አጋጣሚው ውድድሩን ሲከታተሉ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ስሜት በእጉ ተፈታነ፡፡

ወበቃማ በነበረው የአየር ሁኔታ ውሀ ፍለጋ ከመስመሯ ስትወጣ ከተወዳዳሪዎቹ 30 ሜትር የሚጠጋ ራቀች፤ ያኔ ህመሙ የከፋ ደረጃ እንደደረሰ ብዙዎች ገመቱ ተስፋም ቆረጡ። ያለችበትን ርቀት የተረዱት ተመልካቶች በየትኛው ተዓምር ነው ከዚህ ተነስታ ልታሸንፍ የምትችለው? ወርቁ ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ማድረግ የሚችለው ማነው? የሀገሬው ስፖርት ወዳድ ሌሎች አትሌቶችን ማማተር ጀመረ።

የጥሩነሽ ታላቅ እህት እጅጋየሁ ዲባባ፣ አሃዛ ኪሮስ እና መስታወት ቱፋ ሌሎች ኢትዮጵያን የወከሉ አትሌቶች ቢሆኑም ወርቅ የማሳካት ቁመና ላይ አልነበሩም ተብሎ በብዙዎች ይገመት ነበር። መስታወት ቱፋ ወበቁን መቋቋም ተስኗት በውድድር መቀጠል አልቻለችም ውድድሩን አቋረጠች። የእህቷን ህመም እያየች በሮጥ ላይ የነበረችው እጅጋየሁ እና አሃዛ ኪሮስ በጥሩነሽ ደረጃ የሚታይ ብቅት አላቸው ብሎ መቀበል አዳጋች ነው፡፡

ጥሩነሽ ዲባባ ለእርሷ ብቻ ሳይሆን በስፖርቱ ታሪክ ትልቅ ሙገሳ የሚያሰጥ ድል ለማግኘት ዳግም ተነሳች፤ እጅ መስጠት የኢትዮጵያውያን መገለጫ አይደለም፤ ህመም ወደ ኋላ ቢጎትታትም ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር ወደ ውስጧ አልገባም።

ፈተናን ተቋቁሞ ድል ማድረግ እንደሚቻል ቀደምቶቿ ያስተማሯት ኢትዮጵያዊት ናትና፡፡ ምንም እንኳን ለብዙዎች የማይቻል ቢመስልም ቀስ በቀስ መጠጋት ጀመረች። ወደፊት ቀረበች መቅረብ ብቻ አይደለም መገስገሷን ቀጠለች።

የጥሩነሽን መምጣት የተገነዘበችው ለቱርክ የምትሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኤልባን አቢ ለገሰ አቅሟ በፈቀደ ልክ ዙሩን አከረረች፤ ነገር ግን አልተሳካላትም። አሁን ላይ የጥሩነሽ ህመም በድል አድራጊነት ስሜት ተተክቷል፤ እግሮቿን ስታምዘገዝግ ላየ ከህመም ጋር እየታገለች መሆኗን ይጠራጠራል። ውድድሩ ሊጠናቀቅ አንድ ዙር ሲቀረው የጥሩዬ እግሮች እንደተለመደው ማርሻቸውን ቀየሩ። ሀገር በድጋሚ ስሟ በወርቅ አሸበረቀ ባንዲራዋም ከፍ ብሎ ተውለበለበ።

ለትውልድ የሚተላለፍ አንፀባራቂ ድል አሳካች። ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ ጀግኒት ይህ ሩጫ ሀገሬን ወክዬ የማልሮጠው ቢሆን አትጠራጠሩ አቋርጠው ነበር ስትልም ተናገረች። የገጠመኝ የሆድ ህመም ከባድ ነበር፤ የቀጠልኩት ሀገሬን ወክዬ በመምጣቴ ብቻ ነው፤ መቀጠል ብቻ ሳይሆን ውድድሩን ጨርሼ ድል የማድረግ ቁርጠኝነት ያገኘሁት የሀገሬን ሰንደቅ በመያዜ ነው ስትልም ገለፃለች፡፡

በርግጥ በማወራው ልክ ቀላል አልነበረም ትላለች ጥሩነሽ፤ እራሴን በስክሪን ተመልክቼ ከተወዳዳሪዎቹ የነበረኝን ርቀት ሳስብ ውስጤ ማቋረጥን እንደ አማራጭ አይቶም ነበር፤ ነገር ግን ሃገሬን እያሰብኩ በብርታት ቀጠልኩ።

የወከለችኝ እኮ ሀገሬ ናት፤ ወርቁን በማምጣቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ እስካሁን ከገጠሙኝ ውድድሮች በጣም ፈታኙ ውድድር ይህ ነው” በማለት ፅናት ፣ ወኔ ፣ አልበገር ባይነት፣ ለፈተና እጅ አለመስጠትን፣ በአጠቃላይ ለብዙ ነገር ምሳሌ የሚሆነውን ድል ያስገኘችው ጥሩነሽ ዲባባ ከውድድሩ በኋላ ሀሳቧን በዚህ መልክ ገልፃለች።

ጥሩነሽ ዲባባ ስሟን ህያው ያደረገ ድል በጃፓን ኦሳካ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ካመጣች እንሆ 17 አመታት ተቆጥረዋል። ድሉ ጣፋጭ እና የአትሌቷን የፅናት ጥግ ያሳየ በመሆኑ ሁሌም በታሪክ ሲነሳ ይኖራል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review