በማህበራዊ ሚዲያ በተለይ ቲክ ቶክን በመጠቀም ሰዎችን ሲያስፈራራና ሲዝት የነበረው በቲክቶክ ስሙ ቡራ ቡል (Burabull) ወይም ብሩክ ተስፋዬን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
ግለሰቡ ከዛቻ አልፎ በሁለት ሰዎች ላይ አካላዊ ጉዳት ማድረሱም በምርመራ ታውቋል ሲል መምሪያው ለኤ ኤም ኤን የላከው መረጃ ያመላክታል።
እንደ ፖሊስ መረጃ ቡራ ቡል (Burabull) ወይም ብሩክ ተስፋዬ ሰዎችን ስጋት ውስጥ የሚከቱ እና አስደንጋጭ የዛቻ ይዘት ያላቸውን እንዲሁም የፀጥታ አካላትን ስም የሚያጠለሹ መልእክቶችን በቲክቶክ ላይ ሲያሰራጭም ነበር ተብሏል።
ግለሰቡ በሚለቃቸው ህገ-ወጥና ያልታረሙ መልዕክቶች ስጋት ውስጥ የገቡና አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ያቀረቡትን አቤቱታ መነሻ በማድረግ ፖሊስ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ወደ ትግራይ ክልል የሄደ ቢሆንም ከክልሉ ፖሊስ እና ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በቁጥጥ ስር ማዋል እንደተቻለ የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎና ነገር መጠቀም እየተቻለ በተቃራኒው ህዝብን ስጋት ውስጥ የሚከቱ መልዕክቶችን ማሰራጨት ተገቢነት የሌለው ተግባር እንደሆነ ፖሊስ አስታውቆ መሰል ድርጊት የሚፈፅሙ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤ ኤም ኤን የላከው መረጃ ያመላክታል።