የህዳሴ ግድብ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ ውሃ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው

You are currently viewing የህዳሴ ግድብ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ ውሃ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው

AMN ጳጉሜን 1/2017

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአገራችን ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ ውሃ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገለጹ፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በርካታ ውጣ ውረዶችን ተሻግሮ እነሆ ለምርቃት ዝግጁ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያውያን ራሳቸው፤ መሐንዲስ እና የፋይናንስ ምንጭ ሆነው የገነቡት ግድብ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ቦንድ ከመግዛት ጀምሮ የገንዘብ እና የአይነት ድጋፎችን አድርገዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ፤ የሉዓላዊነት ምልክት የሆነው ህዳሴ ግድብ በርካታ መሰናክሎችን አልፎ ለምርቃት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ ያልወጡት ዳገት፤ ያልወረዱት ቁልቁለት፤ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም ሲሉ ሴራቸውን አስታውሰዋል፡፡

በራሳችን ሐብት በመልማት ጽኑ አቋማችን እና ጥበብ በተሞላበት የዲፕሎማሲ ስራ የግድቡን ግንባታ የማስተጓጎል ሴራ ከሽፏል ነው ያሉት፡፡

ይህ እኩይ ሴራ ሊከሽፍ የቻለው በመንግስትና ህዝብ የተባበረ ክንድ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የግድቡ እውን መሆን የቅኝ ግዛት የውሃ ስምምነቶችን በመቃወም የኢትዮጵያን የመልማት መብት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ህዳሴ ግድብ ኢንዱስትሪዎችን በማንቀሳቀስ እና የአገልግሎት ዘርፉን በማዘመን በአገሪቱ እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በአሳ ሃብት ልማት ዘርፍም ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጥ አመላክተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የታችኞቹ ተፋሰስ አገራትን ከጎርፍ እንደሚታደግ እና አመቱን ሙሉ የተመጣጠነ ውሃ እንዲያገኙ እድል እንደሚፈጥር መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review