ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሰላማችንን እያጸናን የኢትዮጵያን የማንሠራራት ጉዞ ለማፋጠን በተባበረ አቅም መትጋት አለብን ሲሉ ገለጹ

You are currently viewing ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሰላማችንን እያጸናን የኢትዮጵያን የማንሠራራት ጉዞ ለማፋጠን በተባበረ አቅም መትጋት አለብን ሲሉ ገለጹ

AMN ጳጉሜን 2/2017

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባስተላለፉት መልእክት ሰላማችንን እያጸናን የኢትዮጵያን የማንሠራራት ጉዞ ለማፋጠን በተባበረ አቅም መትጋት አለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፤

እየተጠናቀቀ በሚገኘው የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያን ታላቁ ህዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ፣ ማዳበሪያ ለማምረት ስምምነት ማድረጋችን፣ የኮሪደር ልማት፣ የአረንጓዴ ዐሻራና ሌሎችም ታላላቅ ስራዎች የተከናወኑበት ዓመት ነው፡፡ እነዚህን እመርታዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል ሠላምን ማፅናት ያስፈልጋል።

ለዚህ ደግሞ ዛሬ የኅብር ቀንን በምናከብርበት ዕለት “ሰላማችንን ማጽናት ለኢትዮጵያ ማንሠራራት” በሚል መሪ ሀሳብ ህብረታችንንና ብዝኃ አቅሞቻችንን በአግባቡ መጠቀምን ያለመ ሀገራዊ መድረክ አካሂደናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ጥለት ህብረ ቀለምና ባለ ብዝኃ ፀጋ ሀገር ናት። የቋንቋ፣ የባህል፣ የእምነት፣ የታሪክ፣ የአመለካከት፣ የጾታ ልዩነት ውበቷና ዕሴቷ ነው። ፀጋዎቻችንን ለብልፅግና ጉዟችን ለመጠቀም “የዘመናት ሾተላይ” ሆኖ የኖረውን የግጭት አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰብረን መጣል የምንችልበት፤ ወሳኝ የታሪክ እጥፋት የምናስመዘግብበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡

የግጭት አዙሪት ምንጭና የብልጽግና ዕንቅፋት የሆኑትን የውጭ ባዳ፣ የውስጥ ባንዳ ለማስወገድ በአንድ እጃችን የብልጽግና ጉዟችንን ማሳለጥ በሌላ እጃችን ደግሞ ሰላማችንን በፅኑ መሰረት ላይ ማፅናት የግድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ማንሠራራት ተጀምሯል፡፡ የዘመናት ስብራቶቿ እየተጠገኑ ናቸው፡፡ ለሁላችን የምትሆን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጸና ኢትዮጵያን ለመገንባት አመራሩ የማስጠበቅ፣ የማጽናት፣ የማሣለጥ እና የማቀናጀት ተግባራትን ሳይቆራረጡ በቀጣይነት በአግባቡ ሊፈጽም ይገባል። በጋራ ጥረታችን የኢትዮጵያን ማንሠራት ወደ ዘላቂ ብልጽግና እናሻግራለን።

የሰላም ሚኒስቴር እና ባለ ድርሻ አካላት ሰላምን ተቋማዊ በማድረግ ወደ ዘላቂ ሰላም የምናደርገውን ጉዞ የመደገፍ ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review