መልከ ብዙዋ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ባህል፣ ማንነት እና ቋንቋዎች ሀገር ናት።
በብዝሃነት ውስጥ የዳበረው ጠንካራው የኅብራዊነት እሴቷ የውበቷ ልዩ መገለጫ ነው። ጳጉሜ 02/2017 ዓ.ም የኅብር ቀን በሚል ተሰይሟል። ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ በሚል መሪ ቃልም እየተከበረ ይገኛል።
ዕለቱን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኮንን አዳራሽ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የጋራ ታሪክ፣ ባህል እና ብዝሃ ማንነት በሚል የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የታሪክ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ፤ ኢትዮጵያ የባህል፣ የንግድ፣ የጋብቻ እና ልዩ ልዩ ትስስር ያለባት ሀገር መሆኗን አመልክተዋል።
በየማህበረሰቡ ያለው ባህላዊ አስተዳደርም ከዘመናዊው አስተዳደር የቀደመ ሲሆን ለዘመዊው ዲሞክራሲ ብዙ የሚያበረክተው እንደሚኖር አንስተዋል። እጅግ የተጋመደው ማህበረሰባዊው እሴት በየዘመናቱ ችግሮች ሲያጋጥሙ የውስጥ ልዩነትን ወደጎን አድርገው ኢትዮጵያን እንዲያስቀድሙ ያስቻለ ነው ብለዋል።
በዚህ ዘመንም በህዳሴ ግድብ ላይ የታየው ጠንካራ አንድነትም የዳበረ የኢትዮጵያውያን ኅብር መገለጫ መሆኑን በፅሁፋቸው ጠቅሰዋል። በየዘመናቱ የዳበረ ሀገራዊ እሴትን የሚሸረሽሩ አጋጣሚዎች ቢፈጠሩም ኢትዮጵያውያን ለልዩነት ቦታ ባለመስጠታቸው ሀገርን ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ ችግር አለመከሰቱን አውስተዋል።
ኅብረብሔራዊት ኢትዮጵያን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማኖር የሚደረገው ጥረት በምክክር ኮሚሽኑ በኩል ፍሬ ሊያፈራ እንደሚችል እምነታቸውን አስቀምጠዋል።

ማህበራዊ ባህላዊ እሴቶች እና ኅብረብሔራዊ አንድነት በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ፅሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር ተካልኝ አያሌው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያላት ሶሻል ካፒታል ወይም ማህበራዊ ሀብት የተለያየ ማህበረሰብ የሚጣመርበት፤ ለወንድማማችነትና ትብብር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልፀዋል።
ከዕድር ጀምሮ ያሉ ማህበራዊ ሀብቶች በመረዳዳት እና ለችግሮች መፍትሔ በማበጀት የሚታወቁ ናቸው። በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት ይህ ማህበረሰባዊው የመደጋገፍ እሴት ጎልቶ ሲታይ ይንፀባረቃል።
አሁን ሶሻል ካፒታልን (ማህበራዊ ሀብት) ለማጎልበት ትልቅ ዕድል አለ ያሉት ዶ/ር ተካልኝ፤ መንግስት እና ፀሀፍትም ለባህላዊ እሴት ሰፊ ቦታ ሰጥተዋል ብለዋል። ብዝሃነት የዚህ ሀገራዊ እሴት ማዕከል በመሆኑም ለህብረብሔር ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው አመላክተዋል።
ሚዲያ አመለካከትን በመቀየር ትልቅ ድርሻ እንዳለው ያነሱት ደግሞ የሚዲያ ሚና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታ በሚል ፅሁፋቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ተስፋዬ በዛብህ ናቸው። ብዝሀነትን በማጎልበት እና በማስተዋወቅ ትልቅ ድርሻ የሚጫተው ሚዲያው በዚያው ልክ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እንደሚኖሩት አንስተዋል።
ከለውጡ ወዲህ የተስተዋለውን የሚዲያ ነፃነትን ጠቅሰው መንግስት ከልክ ያለፉ እና ሀገራዊ አንድነትን የሚጎዳ አካሄድ የተከተሉት መገናኛ ብዙሃንን ለመግራት የወሰዳቸው እርምጃዎችንም አብራርተዋል።
ሀቅ መቆጣጠሪያ ተቋማት አለመኖር፣ የዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ተፅዕኖ፣ ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶች እና የሙያ ውስንነቶት የዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸውም ብለዋል። መገናኛ ብዙሃንን በአግባቡ በመያዝ ለሀገራዊ መግባባት እና ለኅብረብሔራዊ አንድነት ማዋል እንደሚቻልም ነው ዶ/ር ተስፋዬ የገለፁት።
በማሬ ቃጦ