የኢፌዴሪ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ለዘመናት የለፋንበት የኢትዮጵያ ከፍታ ማብሰሪያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት ግድብ ለምርቃት መብቃቱን ጠቅሰው፤ በቦታው ተገኝተው ይህን በማየታቸው እንደ አንድ የሀገር ጦር መሪ ትልቅ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የግድቡ መሠረተ ድንጋይ ሲጣል ጀምሮ ለምርቃት እስከበቃበት ጊዜ ድረስ የቀጠናውን የአየር ክልል በአስተማማኝነት በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ካለፉት ዓመታት በተለየ ሁኔታ ተቋሙ የምድር አየር መከላከል አቅም ማሳደጉን ገልጸው፤ በሰማይ የጠላትን ዒላማ በአስተማማኝ ሁኔታ ገና ከመነሻቸው ማውደም የሚችሉ ተዋጊ የጦር ጄቶችን መታጠቁን ገልጸዋል፡፡
ግዳጅን ባጠረ ጊዜ በላቀ ብቃት የመፈፀም እምቅ አቅምና ቴክኖሎጂውን መጠቀም የሚችል የሠው ኃይል በማደራጀት በማንኛውም ሰዓት የአየር ክልሉን የማያስደፍር የሀገር ኩራት የሆነ አየር ኃይል መገንባቱንም የኢዜአ መረጃ ያመላክታል፡፡