ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ምን ይሰራ?

You are currently viewing ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ምን ይሰራ?

መስከረም አንድ ብሎ ሲጀምር አዲስ ዓመት ሲዘከር ‘የአፍሪካ የእግር ኳስ አባት’ ይድነቃቸው ተሰማ የተወለዱበት ቀን ነውና አብረው ይታወሳሉ፡፡ የእግር ኳስ ተጫዋች፣ አሰልጣኝ፣ አስተማሪ፣ የቡድን መሪ፣ ኮሜንታተር፣ የስነ ልቦና ባለሙያ እና በተለያዩ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የስፖርት መድረኮች መሪ ሆነው ያገለገሉት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ትተው ያለፉት አሻራ ደማቅ ነው።

በ1962 ዓ.ም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ስታስተናግድ እና ዋንጫውን ስታነሳ፣ ይድነቃቸው ተሰማ በአዘጋጅነት እና በቡድኑ ስኬት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። ይህም በወቅቱ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ታሪካዊ ስኬት ነበር። ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራር ላይ በመሆን የሀገሪቱን እግር ኳስ እንዲያድግና እንዲደራጅ አድርገዋል። የሊግ ውድድሮች እና የብሔራዊ ቡድን ዝግጅቶች በተሻለ መንገድ እንዲካሄዱ ትልቅ ጥረት አድርገዋል።

አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያ እግር ኳስ በአፍሪካ ደረጃ ከጠንካራዎቹ ተርታ ይሰለፍ እንደነበር ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። ከተወዳዳሪነት አንጻር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ1962 ዓ.ም የአፍሪካ ዋንጫን በማሸነፍ የአህጉሩ ቀዳሚ ሆኖ ነበር። እንደዚሁም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ሁለት ጊዜ (በ1962 እና 1968 ዓ.ም) በማስተናገድ ስኬታማ አዘጋጅ የነበረች ሲሆን፣ በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ የኢትዮጵያ ክለቦች እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል በየአህጉሩ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ነበሩ።

ለመሆኑ እርሳቸው የደከሙለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ምን ላይ ነው? በዚያን ወቅት የነበሩ ጥሩ ነገሮችን ማስቀጠል ለምን አልተቻለም? በእግር ኳሱ አዲስ ነገር እንዲመጣ ምን ይሰራ? የሚሉና መሰል ጉዳዮችን መጠየቅ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከመሰረተችው ከአህጉራዊና ከቀጣናዊ ውድድርስ ለምን ራቀች? የሚሉት ጥያቄዎችም አሁንም ተገቢውን ምላሽ ሳያገኙ ዓመታት እየነጎዱ ነው፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዙሪያ በመጻፍ የሚታወቁት ኤልያስ አቢ (ዶ/ር)  እንደሚሉት ከሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ልክ እንደ መኪና ፍሬቻ አንዴ ብልጭ አንዴ ድርግም እያለ ለመጓዙ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡ ቀዳሚ ናቸው ያሏቸውን ምክንያቶች ሲጠቅሱም በየትኛውም ዓለም ላይ እግር ኳስ ትልቅ የቢዝነስ ተቋም መሆኑን ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን እግር ኳስ በትክክለኛ ባለሙያዎች ስለማይመራ፣ የአሰለጣጠን ችግር ስላለበት፣ በአካዳሚዎች ግንባታ ላይ ስለማያተኩር፣ አዳጊዎች ላይ ስለማይሰራ እና በሌሎችም ብዙ ምክንያቶች እግር ኳሱ የታመመ ነው ይላሉ፡፡

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ስኬታማ ጉዞ የነበራቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት ያሉትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ “በዓለም ላይ በእግር ኳሱ ስኬታማዎቹ ሀገራት ከኢትዮጵያውያን የተለየ ልዩ ተሰጥኦ አላቸው ብዬ አላምንም” የሚሉት አሰልጣኝ ሰውነት፣ የእግር ኳሳችን ዋነኛው ችግር አስተዳደራዊ ነው ይላሉ። ስራዎች ከታችኛው እርከን ጀምሮ አለመሰራታቸው፣ ኢንቨስትመንታችን የተሳሳተ ቦታ መሆኑና ጠንካራ የእግር ኳስ አካዳሚዎች አለመኖራቸው ለእግር ኳሱ ውድቀት አሰልጣኝ ሰውነት በምክንያትነት ያነሷቸዋል፡፡

በእርግጥም ጉዳዩን አጥብበን በአፍሪካ ደረጃ እንኳን ከተመለከትነው አሁን ላይ ስኬታማ የሆኑ ሀገራት ኢትዮጵያ ካፍን ከመሰረቱ ጥቂት ሀገራት መካከል በነበረችበት ወቅት ብዙዎቹ በቅኝ ግዛት ውስጥ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከቅኝ ግዛት ከወጡ በኋላ ራሳቸውን ችለው እግር ኳስን መምራት ከጀመሩ በኋላና ቀስ በቀስ የቤት ስራቸውን እየሰሩ በመምጣታቸው ስኬታማ መሆን የቻሉ ሀገራት ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ የአፍሪካ ሀገራት ለብሔራዊ ቡድናቸው በቂ እንክብካቤ በማድረጋቸው ተፎካካሪ ቡድኖችን መፍጠር መቻላቸውን ማስተዋል ይቻላል፡፡ አሁን ላይ እንደ ሞሮኮ ያሉ ብሔራዊ ቡድኖችን ከተመለከትን ብሔራዊ ቡድናቸውና ክለቦቻቸው በየዓመቱ የሚያፈሯቸው ወጣት ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ እምነት እንዳላቸው መመልከት ይቻላል፡፡

እግር ኳስ የዕለት ተዕለት እንክብካቤና ስራ ይፈልጋል የሚሉት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ጠቢቡ ሰለሞን በበኩላቸው፣ ዓለም በደረሰበት ደረጃ አስበን መስራት ካልቻልን መቼም እግር ኳሳችንን መለወጥ አንችልም ባይ ናቸው፡፡ ስኬታማ የሆኑ ሀገራት የቤት ስራቸውን እየስሩ ስለመጡ እና እኛ ስላልሰራን መሆኑን አምነን የቤት ስራችንን መስራት ይኖርብናልም ይላሉ። እንደ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ እና ሞሮኮ ካሉ ስኬታማ ሀገራትም ብዙ የሚቀሰም ትምህርት መኖሩን ገልፀው፣ በተለይ ደግሞ በአዳጊዎች ላይ ያለንን እምነት ማሳደግና እነሱ ላይ ሀብታችንን ማፍሰስ ይኖርብናል፡፡ እየሆነ ያለው ግን ይህ አይደለም ሲሉ ይገልጻሉ፡፡

እዚህ ጋር የመምህር ጥበቡን አስተያየት ስጋ ለማልበስ ይረዳን ዘንድ አንድ ማስረጃ ጠቅሰን ማለፉ ተገቢ ይሆናል፡፡ በአሜሪካ ታውሶን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ጋሻው አብዛ (ዶ/ር) በ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን የደመወዝ አከፋፈል አስመልክቶ አደረኩት ያሉት ጥናት ኢትዮጵያ ያላትን ውስን ሀብት ምን ያህል የተሳሳተ ቦታ እያባከነች ስለመሆኑ ፍንጭ የሚሰጥ ነው፡፡ በጋሻው (ዶ/ር) ጥናት መሠረት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ለደመወዝና ጥቅማጥቅም ብቻ በዓመት በአማካይ እያንዳንዳቸው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያወጡ ተጠቁሟል፡፡ ነገር ግን ስንቶቹ ክለቦች የራሳቸው አግር ኳስ ማሰልጠኛ አካዳሚ ኖሯቸው ነው ይህን ያህል ሀብት ፈሰስ እያደረጉ ያሉት? ለሚለው ጥያቄ ግልጽ መልስ ማግኘት አይቻልም፡፡

በእርግጥ ጥናቱ ከተደረገበት በኋላ ባሉት ዓመታትም ቢሆን በእግር ኳሱ ላይ ፈሰስ እየተደረገ ያለው ሀብት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ስላለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እየተነሳ ያለው ጥያቄ ግን ሀብቱ እየወጣ ያለው በትክክለኛው ቦታ ላይ ነው ወይ? የሚል ነው፡፡ ሀብት ፈሰስ መደረግ ያለበት በትክክለኛው ቦታ ላይ የሚለውን ሀሳብ የበለጠ ግልጽ ያደርግልን ዘንድ ወደ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ሴኔጋል ተጉዘን አንድ አስረጅ ጉዳይ እናምጣ፡፡ ሴኔጋል በእግር ኳስ በስኬታማነት ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል ስትሆን ለዚህም እንደዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው በእግር ኳስ አካዳሚዎች ላይ በመስራቷ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የሀገሪቱ አግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ እንደሚያሳው የሴኔጋል አካዳሚዎች ከአውሮፓ ክለቦች ጋር ያላቸው ትብብር የፋይናንስ ምንጭ ነው። ለምሳሌ ‘የጄኔሬሽን ፉት‘ አካዳሚ ከፈረንሳዩ ክለብ ኤፍ.ሲ ሜትስ ጋር የረዥም ጊዜ አጋርነት አለው። ይህ አጋርነት ኤፍ.ሲ ሜትስ ለአካዳሚው የገንዘብና የመሳሪያ ድጋፍ እንዲያደርግ ያስችለዋል። በምላሹም ኤፍ.ሲ ሜትስ ከአካዳሚው ወጣት ተጫዋቾችን የማግኘት ቅድሚያ መብት ያገኛል። አለፍ ሲልም ሴኔጋል የተጫዋቾች አካዳሚዎች ትልቅ ገቢ የሚያገኙት ወጣት ተሰጥኦዎችን ለአውሮፓ ክለቦች በመሸጥ ጭምር ሲሆን፣ ለምሳሌ የሳዲዮ ማኔ እና የፓፔ ማታር ሳር ሽያጭ ለአካዳሚዎቻቸው ከፍተኛ ገቢ ስለማስገኘታቸው ለዚህ ማሳያ ተደርገው ይጠቀሳሉ፡፡

የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች፣ በሴኔጋል የእግር ኳስ ልማት ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ ሌሎች አካላትም አሉ። ለምሳሌ ሪያል ማድሪድ ፋውንዴሽን እና ፒ.ኤስ.ጂ አካዳሚዎች በሴኔጋል ፕሮግራሞችን ከፍተዋል። እነዚህ ፕሮግራሞች ለአካባቢው እግር ኳስ መሻሻል የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ያበረክታሉ። በአጠቃላይ ሴኔጋል በተለያዩ ስትራቴጂካዊ ግንኙነቶች እና ትርፋማ በሆኑ የተጫዋቾች ዝውውሮች አማካኝነት በወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ ገንዘብ እያፈሰሰች ነው። ይህም በሀገሪቱ የረጅም ጊዜ የእግር ኳስ ልማት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሯል።

ለመሆኑ በእነ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ዘመን በእግር ኳሱ ከእነሴኔጋልም ቀድሞ ስመ ጥር የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከተዘፈቀበት ማጥ እንዲወጣ እና 120 ሚሊዮን ህዝብ ያለው ሀገር እንዴት ሲባል ምርጥ 22 ተጫዋቾችን ማፍራት ተሳነው? የሚለው እንቆቅልሽስ እንዲፈታ በቀጣይ ምን ይሰራ? ለዚህም ባለሙያዎቹ ጊዜ የሚፈልግ አድካሚ ስራ ነገር ግን ግልጽ የሆነና ተሞክሮ ውጤት ያመጣ መፍትሔ አለ ይላሉ፡፡

በተገቢው የዕድሜ ክልል ውድድሮች እንዲኖሩ ማድረግ፣ በየአካባቢው፣ በየክለቦቹ አካዳሚዎች እንዲስፋፋ ማድረግና በየእድሜ ክልሉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችም እንዲፈጠሩ በመስራት እግር ኳሱን ማሻሻል ይቻላል፡፡ እንዲሁም በዘፈቀደ ሳይሆን በየጊዜው ምን እንደሰራን ምን ውጤት እንዳመጣን መጠናት አለበት፡፡ ምን አይነት ስፖርቶችን ሰርተን ምን አይነት ውጤት አመጣን? የሚሉት ጉዳዮች ላይ በጥናት ላይ የተመሰረተ ስራ ካልሰራን የትም አንደርስም፡፡ በአጠቃላይ እግር ኳስን ሳይንሰዊ በሆነ መንገድ ማለፉ የግድ ነው የሚለውም የባለሙያዎቹ አስተያየት ነው፡፡

በስፖርቱ ላይ እያወጣን ያለነውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ፍሬውን ለመብላት እንዲቻል የዘርፉ አመራር ያስፈልጋል፡፡ ከታች ጀምሮ የማዘውተሪያ በታዎች ያስፈልጋሉ፤ ትምህርት ቤቶች ላይ መሰራት ይኖርበታልም ይላሉ። ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመፍጠር በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚያነሱት መምህር ጠቢቡ ሰለሞን የክለቦቹም ዋነኛ ትኩረት በተተኪ ወጣቶች ላይ ሊሆን እንደሚገባ ያሳስባሉ። ስለሆነም ከሚሰጠው በጀት ለአዳጊዎች ድጋፍ እንዲውል በትኩረት መስራት አለባቸው፡፡ በሊጉ እየተሳተፉ ያሉት ቡድኖች ክለብ የሚለውን መስፈርት ያሟሉና የራሳቸው ስቴዲየም፣ ገቢ ያላቸው እና በአዳጊ ወጣቶች ላይ ጠንካራ የልማት ስራ የሚሰሩ መሆን እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

#Football

#Soccor

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review