አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በአምስት ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ ዓለም አቀፍ የበረራ አገልግሎት እንዲጀምር መታቀዱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ፡፡
አዲሱ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ትልቅ እመርታ ላይ የሚያደርስ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ በመረቁበት ወቅት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በአዲሱ ዓመት ከሚጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያን የ2018 አዲስ ዓመት በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አዲሱ ዓመት ለመላው ኢትዮጵያውያን፣ ለአየር መንገዱ ደንበኞችና ሠራተኞች የደስታ፣ የፍቅርና የብልፅግና ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነትና ሁሌም በትጋት መስራትን የሚጠይቅ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመንግሥት ድጋፍ፣ በአየር መንገዱና በቦርድ አመራርና በሠራተኞች ትጋት ፈተናዎችን ተቋቁሞ በስኬት መቀጠሉን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ በታታሪነት መሥራትና ስኬት መለያው መሆኑን ጠቅሰው፤ በተጠናቀቀው 2017 ዓ.ም ዕድገቱን በስኬት ማስቀጠሉን አስታውሰዋል፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያና አዳዲስ የበረራ መስመሮችን በመክፈት በከፍታ ላይ መሆኑን በመጥቀስ፤ በ2018 በጀት ዓመት አዲሱን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለማስጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ተነሺ አርሶ አደሮችን ወደ አዲስ ቦታ ለማዘዋወር የቤቶች ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን በመግለጽ፤ ለአውሮፕላን ጣቢያው ግንባታ ፋይናንስ እያፈላለግን ነው ብለዋል፡፡
ዲዛይኑ ያለ የሚገኘው የቢሾፍቱን አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ከአምስት ዓመት በኋላ እ.አ.አ በ2030 ተጠናቅቆ ዓለም አቀፍ የበረራ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያው እጅግ ዘመናዊ ተርሚናል ያለውና ከዓለም ታላላቅ አውሮፕላን ማረፊያዎች ተርታ እንደሚሰለፍ በመጥቀስ፤ አየር መንገዱን ከዓለም ስመ ገናናዎች አንዱ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ይህ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የኢትዮጵያን የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ትልቅ እመርታ ላይ የሚያስቀምጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአየር መንገዱ ራዕይ 2035 ወደ 2040 እየተሸጋገረ እንደሚገኝ በማንሳት፥ አዲሱ ዕቅድ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆንና ለደንበኞች የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ተግባር መገባቱን አመላክተዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ስራ ሲጀምር የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕን ማረፊያም እጅግ ዘምኖ የሀገር ውስጥ በረራን በዓለም አቀፍ የአገልግሎት ደረጃ እንዲሰጥ እንደሚደረግ ማስረዳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
በአዲሱ የ2018 ዓመትም አየር መንገዱ አዳዲስ የበረራ መስመሮችን በመክፈት ለደንበኞች ምቹና ቀልጣፋ የአየር በረራ አገልገሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አብስረዋል።