በኮፕ 30 ላይ የአፍሪካውያን አጀንዳ የሚቀርብበት የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን ጸደቀ

You are currently viewing በኮፕ 30 ላይ የአፍሪካውያን አጀንዳ የሚቀርብበት የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን ጸደቀ

AMN-መስከረም 1/2018

“ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ” በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተጠናቋል።

በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ በብራዚል በሚካሄደው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 30) ላይ የአፍሪካውያን አጀንዳ የሚቀርብበት የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን ጸድቋል፡፡

የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን የተጠናከረ እና ቀጣይነት ያለው የአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ እና የአፍሪካ መር የአየር ንብረት ኢኒሼቲቮችን ማጠናከር ላይ ትኩረቱን ያደረገ የመሪዎች ስምምነት መሆኑ ተገልጿል። የአየር ንብረት ጉባኤውን በጋራ ያዘጋጁት ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት ዛሬ በጋራ መግለጫ አውጥተዋል።

በዚህም የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን የአፍሪካ ህብረትን የአረንጓዴ ልማት እና የአፍሪካ የመሬት ገጽታን መልሶ ማቋቋም የሚደረጉ ድጋፎችን እንዲሁም የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በመግለጫው ተነስቷል፡፡

ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽ ብቻ ሳትሆን የመፍትሄው መሪ ተዋናይ መሆኗን በግልጽ መልዕክቷን ያስተላለፈችበት እንደነበር ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት ባወጡት የጋራ መግለጫ አመላክተዋል።

በተጨማሪም በጉባኤው አፍሪካ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ብቻ ሳትሆን የመፍትሄ ምንጭ እና መሪ መሆኗን ጠንካራ መልዕክት እንዳስተላለፈችበት ነው የተገለጸው።

በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት “Africa Climate Innovation Compact” እና “African Climate Facility” የተሰኙ ኢኒሼቲቮችን ይፋ አድርገዋል።

በዚህም ለሀገር በቀል የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች 50 ቢሊዮን ዶላር ሀብት በየዓመቱ የማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወን ተመላክቷል።

መሪዎቹ በጉባኤው ላይ የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውን የገለጸው የጋራ መግለጫው፥ ፈንዱ እዳን ከሚያሸክሙ ብድሮች ይልቅ የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ጠቁሟል። በጉባኤው ዓለም አቀፍ አጋሮች የፋይናንስ ድጋፎችን ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ዴንማርክ ለግብርና ትራንስፎርሜሽን 79 ሚሊዮን ዶላር እና ጣልያን ይፋ ካደረገችው የ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የአየር ንብረት ፈንድ ውስጥ 70 በመቶው ለአፍሪካ የሚሰጥ መሆኑን ነው መግለጫው ያስታወቀው።

ከዚህ ባለፈም የአፍሪካ ልማት ባንክ፣የአፍሪካ ኢምፖርት እና ኤክስፖርት ባንክ (አፍሪኤግዚም ባንክ)፣ አፍሪካ 50 የተሰኘ የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ማዕቀፍን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ለአፍሪካ አረንጓዴ ኢንዱስትሪ ኢኒሼቲቭ 100 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

በጉባኤው ላይ 25 ሺህ በላይ ልዑካን የተሳተፉ ሲሆን 240 የጎንዮሽ ሁነቶች እና በርካታ አውደ ርዕዮች መካሄዳቸውን ያመለከተው መግለጫው፥ ይህም አፍሪካ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ እና ኢኖቬሽን የተግባር ማሳያ እንደሆነች መታየቱን አመልክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review