የኢትዮጵያን የዘመናት የቁጭት ምንጭ የሆነው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የአባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል።
ኢትዮጵያ ህዝቧን አስተባብራ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ብሂልን እውን ያደረገችበት፣ ለመጪው ጊዜ ፕሮጀክቶች ጉልበት እና ተስፋ ስንቅ የሰነቀችበት የግድቡ መጠናቀቅ፤ ከቁጭት ወደ ችሎ ማሳየት ተሸጋግሯል።
በዛሬው ዕለትም ከአዲስ አበባ ከተማ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች በመስቀል አደባባይ ተገኝተው በግድቡ መጠናቀቅ የተሰማቸውን ደስታ እየገለጹ ይገኛሉ።
በህብረት ችለኛል በሚል መሪ ሀሳብ እየተከናወነ የሚገኝው ህዝባዊ ድጋፍ ግድባችን የአንድነታችና የአብሮነታችን አርማ ነው ፣ ከግድብ ወደ ወደብ ፣ በተባበረ ክንድ የኢትዮጵያ ጉዞ እውን ይሆናል ፣ የጉባ ራዕያችን የቀጣይ ድላችን አይቀሬ ነው እና ሌሎችም መልዕክቶች እየተላለፉበት ነው።

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት ባሳለፍነው ጷግሜን 4 በተካሄደው የግድቡ ምረቃ ስነስርአት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመጪዎቹ አመታት እንደሚጀመሩ ያበሰሯቸው ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የእድገት ግስጋሴ ይበልጥ ለማፋጠን እንደሚረዱ ተነግሯል።
ከ30 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው ፕሮጀክቶች በሀይል አቅርቦት ፣ በመኖሪያ ቤት ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ እና በአፍሪካ ግዙፉ አየር ማረፊያ የመገንባት እቅድ እና ሌሎችም ለበርካታ አመታት የምጣኔ ሀብቱ ማነቆ ሆነው ለሰነበቱ ተግዳሮቶች ምላሽ የሚሰጡ ናቸውም ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግድቡ በተመረቀበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የህዳሴ ግድብን ስላጠናቀቅን እንቆማለን ማለት አይደለም ማለታቸው ይታወሳል።
ከንቲባዋ በመጪዎቹ ጊዜዎች ወደብን ጨምሮ ኢኮኖሚው የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች እያሳካን እንቀጥላለን ሲሉም ተደምጠዋል።
በአሁኑ ወቅት ከመዲናዋ የተለያየ ክፍል ከሌሊት ጀምሮ ወደ መስቀል አደባባይ የተመመው ነዋሪ በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ፣ በተለያዩ የባህል አልባሳት እና መፈክሮች ደምቆ ደስታውን እየገለጸ ይገኛል።
በዳዊት በሪሁን