AMN – መስከረም 6/2018 ዓ.ም
ቀደም ሲል በየትምህርት ቤቱ የችግረኛ ቤተስብ ልጆች ባዶ ምሳ ዕቃ ይዘው በመሄድ ከረሀቡ በላይ ለሥነ ልቦና ጫና ይዳረጉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፤ አሁን ላይ በምገባ መርሀ ግብሩ ይህን አስከፊ ችግር መቀየር ተችሏል፡፡
በቀን እስከ 1 ሚሊዩን የሚጠጉ ተማሪዎች እዛው ትምህርት ቤት ውስጥ በቀን 2 ጊዜ ቁርስና ምሳ መመገብ ችለዋል ለውጤታቸው መሻሻልም ትልቅ አስተዋፆኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪችን ጨምሮ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ለሚሆኑ ተማሪዎች በየአመቱ የትምህርት ቤት አልባሳት (ዩኒፎርም) እና የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ይደረጋል፡፡
ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ትውልድ ላይ መሰረት ሊሆን የሚችል ሥራ መስራት ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል፡፡
ሌላው በአዲስ አበባ ከተማ ከሚከናወኑ ሰው ተኮር ሥራዎች መካከል ሀገርን በተለያዩ ዘርፎች በመሰማራት ሲያገለግሉ የነበሩና አሁን ላይ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ አዛውንቶችን መንከባከና መደገፍ አንዱ ነው፣ ለዚህም እነዚህን ወገኖች በየቀኑ መመገብ የሚያስችሉ 26 የምገባ ማዕከላት ተገንብተዋል፤ ባለሃብቶችን ጭምር በማስተባበር በቀን 1 ጊዜ ጥራት ያለው ምግብ መመገብ እንዲችሉም ተደርጓል፡፡
ሌላው አቅመ ደካሞችን ለመደገፍና ለመንከባከብ በተከናወነ ተግባር 4ዐ ሺህ የሚጠጉ የአዛውንት አቅመ ደካማ ቤቶችን በማደሰ ዘመናዊ አኗኗር ዘይቤን እንዲከተሉ እና ከንጽህና ጉድለት ጋር ተያይዞ ይፈጠሩ የነበሩ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል ተችሏል፡፡
ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ከተማ ኑሮአቸውን ጐዳና ላይ ያደረጉና ለጐዳ እና በሴተኛ አዳሪነት ተሰማርተው ኑሮአቸውን የሚገፉ ሴቶችን ችግር ለመቅረፍ በተሠራው ሥራም፣ ለነገዋ የተሃድሶና ክህሎት ማብልፀጊያ ማዕከልን በማቋቋም 1 ሺህ 66ዐ ሴቶች ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራ እንዲሠማሩ በማድረግ የተሻለ ኑሮ እንዲሮሩ ተደርጓል፡፡
በቀጣይ ለነገዋ የተሃድሶና ክህሎት ማብልፀጊያ ማዕከል በዚህ መልኩ ለጐዳና ኑሮ የተጋለጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል፡፡
በበረከት ጌታቸው