ማንችስተር ሲቲ ታሪካዊ ተጫዋቹን በተቃራኒ የሚገጥምበት ጨዋታ

You are currently viewing ማንችስተር ሲቲ ታሪካዊ ተጫዋቹን በተቃራኒ የሚገጥምበት ጨዋታ

AMN-መስከረም 08/2018 ዓ.ም

በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ማንችስተር ሲቲ ናፖሊን በኢትሃድ ሲያስተናግድ ታሪካዊ ተጫዋቹን በተቃራኒ ይገጥማል፡፡

ከ10 ዓመት ቆይታ በኋላ ማንችስተር ሲቲን የለቀቀው ኬቨን ደብሩየና ዛሬ ምሽት ወደ ኢትሃድ ይመለሳል፡፡ በክረምት የተጫዋቾች ዝውውር የአንቶኒዮ ኮንቴ ናፖሊን የተቀላቀለው ቤልጄማዊ ታሪክ የሰራበትን ክለብ በተቃራኒ ይገጥማል፡፡

የ33 ዓመቱ ተጫዋች በሲቲ ቆይታው 422 ጨዋታ አከናውኖ 108 ግቦችን አስቆጥሮ ወደ ግብነት የተቀየሩ 170 ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡ በውሃ ሰማያዊ መለያ 16 ዋንጫዎችንም አሸንፏል፡፡ በናፖሊ በኩል ለማንችስተር ከተማ አዲስ ያልሆኑት የቀድሞ የዩናይትድ ተጫዋቾች ስኮት ማክቶሚኔይ እና ራስመስ ሆይሉንድም በደንብ ወደ ሚያውቁት ከባቢ ይመለሳሉ፡፡

በጨዋታው በሲቲ በኩል ኧርሊንግ ሃላንድ ልዩነት ፈጣሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የ24 ዓመቱ አጥቂ የውድድር ዓመቱን እንደተለመደው በግብ ታጅቦ ጀምሯል። ኖርዌያዊው አጥቂ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ያለው የግብ ክብረወሰን ምን ዓይነት አጥቂ እንደሆነ ያሳያል።

49 ግቦችን ያስቆጠረው በ48 ጨዋታዎች ብቻ አከናውኖ ነው። በቻምፒየንስ ሊግ 50 ግብ ለማስቆጠር ትንሽ ጨዋታ የወሰደበት ኔዘርላንዳዊው አጥቂ ሩድ ቫንስተልሮይ እንደሆነ የኦፕታ መረጃ ያሳያል።

የቀድሞ የማንችስተር ዩናይትድ እና ሪያል ማድሪድ አጥቂ 50 የቻምፒየንስ ሊግ ግብ ላይ ለመድረስ 62 ጨዋታዎችን ማከናወን ነበረበት። ሌላው ትኩረት የሚስበው ጉዳይ የሁለቱ አሰልጣኞች ፍጥጫ ነው።

ፔፕ ጋርዲዮላ እና አንቶኒዮ ኮንቴ ዛሬ ለስምንተኛ ጊዜ ይገናኛሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው ሰባት ግንኙነት ጣልያናዊው አሰልጣኝ አራት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይወስዳል። ፔፕ በኮንቴ የተመራውን ቡድን ሦስት ጊዜ መርታት ችሏል።

ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ አራት ጊዜ ተገናኝተው ሲቲ ሁለቱን ሲያሸንፍ ናፖሊ በአንዱ ድል ቀንቶታል። ናፖሊ በአውሮፓ ውድድሮች ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር ባደረጋቸው 12 ከሜዳ ውጪ ጨዋታ በአንዱም አላሸነፈም። ዛሬ አዲስ ታሪክ ለመፃፍ በኢትሃድ ይፋለማል።

በሌላ ተጠባቂ ጨዋታ ኒውካስትል ዩናይትድ በሜዳው ሴንት ጀምስ ፓርክ ባርሰሎናን ያስተናግዳል። ባርሰሎና ላሚን ያማልን በጉዳት አያሰልፍም። አሌሃንድሮ ባልዴ እና ጋቪም ጉዳት ከስብስቡ ውጪ አድርጓቸዋል።

በአዲስ ፈራሚው ኒክ ቮልትማደ ብቸኛ ግብ የሊጉን የመጀመሪያ ድል ወልቭስ ላይ ያገኘው ኒውካስትል ከ22 ዓመት በኋላ ባርሴሎናን ይገጥማል። ሁለቱ ክለቦች በአጠቃላይ አራት ጊዜ ሲገናኙ ሦስቱን የካታላኑ ክለብ አሸንፏል። ኒውካስትል ዩናይትድ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል።

ሁለቱም ተጠባቂ ጨዋታዎች ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይጀምራሉ። በሌሎች ጨዋታዎች ፍራንክፈርት ከ ጋላታሳራይ ፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን ከ ኪራት አልማቲ ጋር በተመሳሳይ 4 ሰዓት ይጫወታሉ።

ምሽት 1:45 ክለብ ብሩጅ ከ ሞናኮ ፣ ኮፐንሀገን ከ ባየር ሊቨርኩሰን ጨዋታቸውን ይጀምራሉ።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review