የህብረተሰቡን የኑሮ ሸክም የሚያቃልሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችንና ሰው ተኮር የልማት ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing የህብረተሰቡን የኑሮ ሸክም የሚያቃልሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችንና ሰው ተኮር የልማት ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ገለጹ

AMN- መስከረም 8/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 የሚገኙ 15 የአቅመ ደካማ ቤቶችን እድሳት አጠናቆ የምረቃና ርክክብ መርሃ ግብር አካሂዷል።

በምረቃና ርክክብ መርሃግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር)፣ ባለስልጣኑ ከትምህርት ጥራት ቁጥጥር ስራዎች ባሻገር የህብረተሰቡን ሸክም በሚያቃልሉ መሰል የበጎ ፈቃድ ሰራዎች መሰማራቱን አድንቀው፣ ተግባራቱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኢዘዲን ሙስባህ በበኩላቸው፣ የአቅመ ደካማ ቤቶች እድሳት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገባቸው ገልጸው፣ በባለስልጣኑ የ90 ቀናት እቅድ መከናወናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ፣ ሰው ተኮር በሆኑ ልማት እቅዶች በክፍለ ከተማው በሶስት ወራት ውስጥ ከ420 በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች በተመሳሳይ ተገንብተው እያስረከብን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የቤቶችን እድሳትና ግንባታ ለማከናወን የገንዘብ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ተቋማትና ግለሰቦች በመርሃ ግብሩ ላይ እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የቤት እድሳቱ ተጠቃሚ የሆኑ አቅመ ደካሞች በበኩላቸው፣ በተደረገላቸው በጎ ተግባር መደሰታቸውን ገልፀው፣ ምስጋና አቅርበዋል።

ግንባታና እድሳት ተደርጎላቸው ለአቅመ ደካሞች በተላለፉ 15 ቤቶች ውስጥ 111 የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ መሆናቸውም ተገልጿል።

በይታያል አጥናፉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review