ኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 2029 ወይም 2031 ለማዘጋጀት ለዓለም አትሌቲክስ ጥሪ ማቅረቧን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቋል።
ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ፍላጎት ላላቸው ሃገራት በቶኪዮ በተዘጋጀው የኦብዘርቨር መርሃግብር ላይ ከመንግስትና ከፌዴሬሽኑ የተወጣጡ አመራሮች ተካፍለዋል።
ኢትዮጵያ እድሉ ከተሰጣት የስፖርት መሰረተ ልማቶችን በበቂ ሁኔታ በማሟላት ውድድሩን የማስተናገድ አቅሟን ታሳያለች ሲሉ የባህል እና ስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መክዩ መሐመድ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም አትሌቲክሱ ላይ ሰፊ ስራ በመስራት ወደ ነበረው ከፍታ እና መነቃቃት ማድረስ እንደሚገባም አንስተዋል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ለሻምፒዮናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተሻለ መልኩ ኢትዮጵያ ላይ ይገኛል ብሏል።
ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ካዘጋጁ ሀገራት ያላቸውን ልምድ ለመካፈል በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁሟል።