ኪነ ጥበብ ማህበረሰብን በማንቃት፣ በማስተማር፣ ለእድገት በማነሳሳት እና በመምራት በኩል አይተኬ ሚና አለው። ለለውጥ የመጓጓት እና ቁጭትን በመፍጠር ለተሻለ የወደፊት ዕድል ትልቅ አቅም ይፈጥራል። ይህ እውነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመገንባቱ በፊት እና ግንባታው ከተጀመረ በኋላም የታየ ነገር ነው፡፡
የግድቡ ግንባታ ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ በተለይ ምሳሌያዊ አነጋገሮችና ሙዚቃዎች የአባይ ወንዝን በተመለከተ በቁጭትና በብስጭት የተሞሉ ነበሩ። በርካታ ታዋቂ አርቲስቶችና ገጣሚዎች ዓባይ የሀገራችንን የተፈጥሮ ሃብት ይዞ ወደ ሌላ ሀገር የሚፈስ መሆኑን በስራዎቻቸው ሲገልፁ ቆይተዋል።
ይህ ስሜት ዘመናትን በተሻገሩ ተወዳጅ ስራዎች ተንፀባርቋል። የኢትዮጵያ ህዝብ “የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው” እያለ ለዘመናት የዓባይን ስጦታ ከመጠቀም ይልቅ ብዙ እያጣ እንዳለ ይሰማው የነበረውን ስሜት በኪነ ጥበብ ስራዎች ውስጥ በግልጽ ተንጸባርቋል፡፡
ከዚህም ባሻገር “የራሳችን ወንዝ በባእድ ሀገር ምን ይሰራል? ዓባይ ማደሪያ የሌለው ከሚል ወጥቶ መቼ ነው በሀገሩ ኢትዮጵያ ሚያድረው” በሚል ጥያቄ ላይ ያተኩሩ የጥበብ ስራዎችም ሲሰሩ ቆይተዋል።
የሚበሉት ውሃ የሚጠጡት ውሃ
ዓባይ ለጋሲ ነው በዚያ በበርሃ
አንተ ወራጅ ውሃ ቢጠሩህ አትሰማ
ምን አስቀምጦሀል ከግብፆች ከተማ….እንዳለችው ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፡፡
የግድቡ ግንባታ ሲጀመር፣ ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብም አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። ከዚያ በኋላ የሙዚቃ ይዘት ከቁጭት ወደ የተስፋ፣ የኩራትና የጋራ ማንነት ስሜት እንዲሁም ህዝቡን ወደ ማነቃቃት ተሸጋገረ። ቀደም ሲል ዓባይን “ከሀገሩ፣ የሀገሩን ወርቅና አፈር ይዞ የሚያመልጥ” አድርገው ይገልፁ የነበሩ ሙዚቃዎች፣ አሁን ደግሞ “የኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረትና ድል ምልክት” አድርገው ማሳየት ጀመሩ።
“እንጉርጉሮ ይብቃ ይገባል ውዳሴ
ጉዞውን ጀምሯል ዓባይ ለሕዳሴ
ትውልድ እንደ ጅረት የተቀባበለው
ቁጭት ፀፀት ሥጋት ዛሬ ሊቋጭ ነው…” ተብሎ ተዘመረ፡፡
በርካታ አርቲስቶችና ሙዚቀኞች የህዝቡን አንድነት፣ ለግድቡ ያለውን ፍቅርና የገንዘብም ሆነ የጉልበት አስተዋፅኦ በተመለከተ የኪነ ጥበብ ስራዎችን መስራት ጀመሩ። ይህ ደግሞ ህዝቡን በግድቡ ፕሮጀክት ዙሪያ የበለጠ እንዲተባበርና የአንድነት መንፈስ እንዲሰማው አድርጓል። በዚህ ለህዳሴ ግድብ ህዝብን በኪነ ጥበብ ማነቃቃት፣ ማስተማርና ቦንድ የመሸጥ መርኃ ግብር ላይ በንቃት ከተሳተፉ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ውስጥ አንዱ ቻቻ (የኪፍያፍ) ነው፡፡
የኪፍያፍ የግጥምና ዜማ ደራሲ እንዲሁም የቴአትር ባለሙያ ሲሆን በኪነ ጥበብ አማካኝነት ማህበረሰቡን ለማነቃቃትና ለማስተባበር በአራቱ የኢትዮጵያ ማዕዘናት በርካታ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ የህዳሴ ግድብን የተመለከተ “አውሽ” የተሰኘ ዶክመንተሪም አበርክቷል፡፡
ቻቻ እንደሚለው የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የተሰራው የኪነ ጥበብ ስራ በኢትዮጵያ የእድገት ጉዞ ውስጥ ከታዩ አስደናቂ ታሪካዊ ሁነቶች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ታሪክ የማይዘነጋው ደማቅ አሻራ ነው፡፡ የኪነ ጥበብ ባለሙያው ከማዝናናትም ያለፈ ድርብ ኃላፊነቱን የተወጣበት ወቅት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ምክንያቱም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ስንዞር ማዝናናት ብቻም ሳይሆን በ8100 አማካኝነት ገንዘብ እናሰባስባለን፡፡ ቦንድ እንሸጣለን። በተጨማሪም እንደየአካባቢው ማንነት ባህሉን በማጥናት የሚያነቃቁ የጥበብ ስራዎችን እናቀርባለን፡፡ ይህም በማህበረሰቡ ዘንድ ቁጭት እንዲፈጠር ያደረገ ነበር ይላል፡፡ እስኪ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ማነቃቂያነት ከዋለው የራሱ ስራ ውስጥ ጥቂት ስንኞችን እንጥቀስ፡-
ኩነኔ አለበት መዳፌ፣
ጉርሻ ነስቼ ላፌ፡፡
ባንተ ኑሪያለሁኝ ቅኔ ዘርፌ፣
ኦሮማይ ኦሮማይ ነቃሁ ከእንቅልፌ፡፡
…የአዳም ቀዳማዊ ምላስ ማርጠቢያ
የገነት እግር አጥንት ሔዋን አፈርያ፡፡
በአስዋን ቄራ የውሃ ፍሬ
የብርሃን አዝመራ
በቤኒ ሻንጉል ጎተራ…፡፡
ይህ የቻቻ ስራም ሆነ ሌሎች ከግንባታው መጀመር በኋላ የተሰሩ የኪነ ጥበብ ስራዎች የአባይን ወንዝ አስመልክቶ የነበረው ብስጭትና ቁጭት ወደ ኩራትና የጋራ ድል መለወጡ ማሳያ ተደርገው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ኪነ ጥበብ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ይፋ ከመደረጉ በፊት የነበረውን የቁጭት ስሜት እንደመስታወት ያሳየ እንደነበር ሁሉ፣ ከፕሮጀክቱ በኋላ ደግሞ የተስፋና የኩራት ድምጽ ሆኗል።
ቻቻ ግድቡ መጠናቀቁ የፈጠረብኝ የደስታና የኩራት ስሜት እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ የሚጠቅም ነገር በማድረጉ የሚሰማው ስሜት ተሰምቶኛል፡፡ ዓባይ የአባቶች፣ የእናቶች፣ የልጆች የትውልዱና የመሪዎቻችን ቁጭት ነበር፡፡ እናም “ይህን ታሪክ ሰራ” የሚባለው የዚህ ትውልድ አካል በመሆኔ እኮራለሁ” በማለት ስሜቱን ያጋራል፡፡
በተጨማሪም ሀገሬ ከግድቡ የምታገኘውን ጥቅም ሳስብ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ኢትዮጵያ የዘመናት ኢ-ፍትሐዊ ታሪክን በማሸነፍ ያገኘችው ገድል፣ በልዩነት ውስጥ ለዓለም ያሳየነው አንድነትና ትብብር ጥልቅ የደስታ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል በማለት ያብራራል፡፡
አሁን ግድቡ በብዙ ውጣ ውርድ አልፎ የምርቃት ሪቫኑ ተቆርጧል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚጠበቀው ቀጣይ ስራ ምን መሆን አለበት የሚለውን ሃሳብ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡
የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የግድቡን አነሳስ፣ የግንባታ ሂደት እና በሂደቱ የነበሩ ፈተናዎች እና ድሎችን የሚተርኩ ፊልሞችን፣ ሙዚቃዎችን፣ ዘጋቢ ፊልሞችን እና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎችን መስራት ይችላሉ። ይህ ታሪኩን ለብዙሃኑ ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር፣ የግድቡን ብሔራዊ ጠቀሜታ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ለልማት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ግድቡ የኢንጂነሪንግ ጥበብ እና የተፈጥሮ ውበት ጥምረት ነው። ፎቶ ግራፍ አንሺዎች እና ሰዓሊዎች የግድቡን ግዙፍነት፣ በዙሪያው ያለውን ተፈጥሮ እና የግንባታ ሂደቱን የሚያሳዩ ፎቶ ግራፎችን እና ስዕሎችን በመስራት ለህዝብ ማሳየት ይችላሉ። እነዚህ ስራዎች በኤግዚቢሽኖች እና በኪነ ጥበብ ጋለሪዎች ላይ ሊቀርቡ ይችላሉ።
የኪነ ጥበብ ባለሙያው ቻቻ የህዳሴ ግድብን የተመለከቱ የኪነ ጥበብ ስራዎች በቀጣይ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ ሀገር በቀል የኪነ ጥበብ እውቀትን ለሀገር በቀል እድገት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ስነ ጽሑፋዊ ብዝሃነትን ማክበር ይገባል በማለት ያብራራል፡፡
በጊዜው አማረ