የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለብቁና የሰለጠነ ሰው ኃይል ግንባታ የሰጠው ትኩረት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱንና የከፍታ ጉዞውን ይበልጥ ለማጠናከር የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ገለፁ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ፣ በአውሮፕላን ጥገና፣ በበረራ አስተናጋጅነትና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ያሠለጠናቸውን 1 ሺህ 103 ተማሪዎች አስመርቋል።
ከተመራቂዎች መካከል ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ በርካታ ሰልጣኞችም ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ባስተላለፉት መልዕክት፥ አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ከፍታ አስጠበቆ ለማስቀጠል የሰው ሀብት ልማት ዋነኛ ምሰሶ ነው ብለዋል።
አየር መንገዱ በበረራ ኢንዱስትሪው ያለውን የገዘፈ ሚና ይበልጥ ለማጠናከር በሁሉም መስክ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህም አንዱ የሰው ኃይል ግንባታ መሆኑን በማንሳት፥ በሀገር ውስጥ ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ከማፍራት በተጓዳኝ የተለያዩ የውጭ ሀገራት ዜጎችን በማሰልጠን ልምዱን እያካፈለ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ደህንነት፣ ትክክለኝነትና፣ የደንበኞች አገልግሎት የአቪየሽን ኢንዱስትሪው ቁልፍ ጉዳዮች በመሆናቸው ሰልጣኞች ወደ ስራ ዓለም ሲሰማሩ እነዚህን እሴቶች መተግበር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው አየር መንገዱ በአፍሪካ እና በዓለም ተመራጭና አስተማማኝ የበረራ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በሁሉም መስክ ስኬታማ ሥራ በማከናወኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከታታይ እውቅናዎችን እያገኘ ነው ማለታዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ብቁ ሙያተኞችን በማሰልጠን የአህጉሪቱን የበረራ ኢንዱስትሪ በማሳደግ ረገድ መሪ ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።