ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተጀመረውን ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ለማፋጠን ዲጂታል አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
“ጠንካራ የመንግስት ኢንቨስትመንት ሥርዓትና የመረጃ ጥራት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ በባህርዳር ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ እንደሀገር ልማትን በማጠናከር ድህነትን ታሪክ ለማድረግና ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባትና ኢንቨትስትመንትን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በማጠናከር የተጀመረውን ሀገራዊ ብልጽግና ለማፋጠን ዲጂታል አሰራርን መከተል ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ለዚህም ጠንካራ የመንግስት የኢንቨስትመንት ስርዓትና የመረጃ ጥራት ግንባታ ላይ በትኩረት መስራትና ሁለንተናዊ የልማት ሥራውን በዲጂታል አሰራር ማገዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው፣ የክልሉ መንግስት በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ መሻሻል ከማሳየት ባለፈ ዲጂታል ትግበራን ጨምሮ ሌሎች የእድገት መሰረት የሆኑ አሰራሮችን አስቀድሞ ተግባራዊ አድርጓል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በኢንቨስትመንት፣ በዲጂታል፣ በዕቅድና በሪፖርት አቀራርብ ላይ ያመጣቸውን አዳዲስ አሰራሮች በትክክል መተግበር ከተቻለ በሀገር ደረጃ ወጥ አተገባበር እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡