ማንችስተር ዩናይትድ ባሳለፍነው ቅዳሜ በብሬንትፎርድ ከተሸነፈ በኋላ በድጋሚ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ላይ የሚነሱ ትችቶችም የበለጠ ገዝፈዋል፡፡
ቢ ቢ ሲ ላይ በትንተና እየሰራ የሚገኘው የማንችስተር ዩናይትድ የቀድሞ ታላቅ ተጫዋች ዋይን ሩኒ የሰላ ትችት ሰንዝሯል፡፡
በ13 ዓመት የዩናይትድ ቆይታው የከፍታውን ዘመን ብቻ ያየው ሩኒ ’’በክለቡ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለመረዳት ከብዶኛል፡፡’’ ሲል ተናግሯል፡፡
’’አሞሪም ወጣት አሰልጣኝ ነው ፤ ከፊቱ ብሩህ ጊዜ ይጠብቀዋል፡፡ በዩናትድ እየሰራ ያለው ስራ ግን ከብዶታል፡፡’’ በማለት ገልጿል፡፡
የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ እና የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን ጨምሮ 16 ዋንጫዎችን ከቀያይ ሰይጣናቱ ጋር ያሸነፈው እንግሊዛዊው የቀድሞ አጥቂ ክለቡ እየሄደበት ያለውን አቅጣጫ ለመናገር ይከብዳል ብሏል፡፡
ተጫዋቾች በፍላጎት ሲጫወቱ ፣ ሲፋለሙ ፣ የሚመጣውን ጫና ሲሸከሙ አልተመለከትኩም ያለው ዋይን ሩኒ ይህን ማንችስተር ዩናይትድ አላውቀውም ሲል ቢ ቢ ሲ ላይ በነበረው ዝግጅት ሃሳቡን ሰንዝሯል፡፡
አሁን ክለቡ ያለበት ሁኔታ እንደሚያበሳጨው የገለፀው ሩኒ የክለቡ አስተዳዳሪዎች አቅጣጫቸውን በግልፅ ማሳወቅ አለባቸው ሲል ተናግሯል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ