ኢትዮጵያ የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ መዳረሻዎች ያሏት መሆኗን የውጭ ሀገር ጎበኚዎች ገልፀዋል። ኢትዮጵያ ያሏትን እምቅ የተፈጥሮና ታሪካዊ ቅርሶች ለመጎብኘት በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን የላቁ የውጭ አገር ዜጎች ወደ አገሪቱ ይተማሉ፡፡
ጎብኚዎቹ በአብዛኛው በዩኔስኮ የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ እንዲሁም በምዝገባ ሂደት ላይ ያሉ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶችን መጎብኘት ምርጫቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ለሁለተኛ ጊዜ የመጡት አሜሪካዊው ቱሪስት ማርኪያ ዳርም በመጀመሪያ ጉብኝታቸው የላሊበላ ወቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የጥምቀት በዓል አከባበርንና የኦሞ ሸለቆን መመልከታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከረገጡበት ቀን አንስቶ የተመለከቱት የማህበረሰቦች ባህልና እሴት እንዲሁም የማይረሳ መስተንግዶ በድጋሚ እንዲመጡ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡
በቀደመ ቆይታቸው ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ባህል፣ ታሪክ፣ ቅርስና የተፈጥሮ መስህብ መመልከታቸውን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ አውስትራሊያዊው ኒክ ድን በበኩላቸው በኢትዮጵያ በነበራቸው የቆይታ ጊዜ የኦሞ ሸለቆና ሌሎች መዳረሻዎችን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጎበኟቸው አካባቢዎች አስደናቂ የማህበረሰብ አኗኗር፣ ባህልና እሴት በመመልከት የማይረሳ ልምድ መቅሰማቸውን ተናግረዋል፡፡ ስፔናዊው ፓብሎ ዊድን እንደገለጹት በኢትዮጵያ ዓይን የሚማረኩ፣ የውስጥ እርካታ የሚሰጡና መንፈስን የሚያድሱ ባህላዊና ታሪካዊ የተፈጥሮ መስህቦችን ጎብኝተዋል፡፡

ጎብኝዎቹ ኢትዮጵያ እምቅ የሆነ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መዳረሻ የታደለች ሀገር መሆኗን ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች መኖራቸውን ጠቅሰው በተለይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ያላቸው ቅርሶች፣ ቅሪተ አካላትና የጥናት ግኝቶች መኖራቸውን ጎብኝዎቹ ገልጸዋል፡፡
ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ያደረጉት ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ወይዘሮ ወርቅነሽ ዘውዴ ዘወትር ወደ አገራቸው ሲመጡ አዲስ ስሜት እንደሚፈጠርባቸው ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የተለያዩ ቅርሶች፣ ታሪኮች ባህሎችና የተለየ የአየር ጸባይ የተላበሰች ውብ አገር መሆኗንም ተናግረዋል፡፡